የሲስት ህመም እንዴት ይከሰታል? ህመሙንስ እንዴት መከላከል ይቻላል?

You are currently viewing የሲስት ህመም እንዴት ይከሰታል? ህመሙንስ እንዴት መከላከል ይቻላል?
  • Post category:ጤና

‎AMN – መስከረም 22/2018 ዓ .ም

‎ሲስት ከ 12 አመት ጀምሮ የሚገኙ ታዳጊ ሴቶች ላይ ሊከሰት የሚችል የህመም አይነት መሆኑን የዘርፉ ባለሞያዎች ይናገራሉ። የወር አበባ የምታይ ሴት በየወሩ የሚለቀቅ እንቁላል መኖሩ ይታወቃል።

እንቁላሉ ከተለቀቀ በኃላ እንቁላሉን ይዞት የነበረው ከረጢት ውሀ በመቋጠሩ ምክንያት የሚከሰተው ህመም ሲስት እንደሚባል በግሩም ሆስፒታል የማህፀን እና ፅንስ ስፔሻሊስት እንዲሁም የፅንስ እና የእናቶች ሰብ ስፔሻሊስት ሀኪም ዶ/ር ቴዎድሮስ ዝናቡ ይገልፃሉ ።

‎ሲስት ህመም በብዙ ምክንያቶች እንደሚከሰት የገለፀው ስፔሻሊስቱ፣ የመጀመሪያው የወር አበባ ኡደት ላይ የሚከሰት ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የካንሰር ምልክት ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ።

‎ሲስት የካንሰር የሚሆንበት በዘር ወይም በቤተሰብ ሊመጣ እንደሚችል ገልፀው ፣ በኬሚካሎች እና በጨረሮች ተጋላጭ የሆኑ እንስቶች ሊከሰት እንደሚችል ተናግረዋል።

‎ህመሙ ሲከሰት የተለያዩ ምልክቶች ያሉት ሲሆን፤ ከፍ እያለ ሲመጣ ከእንብርት በታች የሆድ ህመም፣ ህመም የሚሰማቸው ቦታ በእጅ ሆድ ሲነካካ እብጠቱ ሊታወቅ እንደሚችል ዶ/ር ቴዎድሮስ ይናገራሉ።

‎ከዚህ በተጨማሪ የወር አበባ ሲመጣ ከፍተኛ የሆነ የሆድ ህመም አንዳዶች ደግሞ የወር አበባ እንደሚያዛባባቸው አስረድተዋል። በዚህ ሁኔታ ላይ የሚገኙ እንስቶች ህመም የሚሰማቸው ቦታ በአልትራሳውንድ ሲታይ ሲስት መሆኑ ሊታወቅ እንደሚችል ዶ/ር ቴዎድሮስ ዝናቡ ገልፀዋል፡፡

‎የሲስት ህመም ህክምናው ምንድ ነው? ‎ለዚህ ህመም ህክምናው እንደ ሲስቱ ባህሪ የሚወሰን ሲሆን፣ በወር አበባ ጊዜ የሚከሰተው ሲስት ምንም ህክምና እንደሌለው እና በየሶስት ወሩ መጠኑ መቀነሱን፣ በአልትራሳውንድ እንደሚታይ ተናግረዋል ።

‎ካንሰር ደረጃ ያልደረሱ ሲስት ሲሆን ደግሞ እንደ ሴቷ እድሜ ወልዳ የመጨረስ ሁኔታ ታይቶ ሲስቱን ማውጣት እስከ የማህፀን የማውጣት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል ብለዋል።

‎ይህ የሚሆነው እንደ ግለሰቦች ሁኔታ የሚወሰን መሆኑን ገልፀው፣ እንደየሁኔታው ካንሰር የሆነባቸው ደግሞ የኬሞ ቴሪፒ ክትትል የሚደረግላቸው መኖራቸውን አስረድተዋል።

‎ሲስትን እንዴት መከላከል ይቻላል?

‎ሲስት የሚከሰትበት ምክንያት በግልፅ ስለማይታወቅ መከላከል አይቻልም ብለዋል። ስለዚህ ህመም ሲከለት የህክምና ክትትል ማድረግ እና የማህፀን ካንሰር የተያዘች እናት ወይም ሌላ የቤተሰብ ታሪክ ካለ በየጊዜው ወይም አመታዊ ምርመራ ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።

‎ሲስት በየትኛው እድሜ ላይ ይከሰታል?

‎እንደ ዶ/ር ቴዎድሮስ ገለፃ፣ የተለያየ አይነት የሲስት ባህሪ ስላለ 12 ዓመት እድሜ ያላቸው ታዳጊዎች ጭምር የሲስት እጢ ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ።

‎ሲስት በእድሜ የተገደበ የህመም አይነት ባይሆንም፣ በተለይ ወደ ካንሰር የማደግ እድሉ ሰፊ የሆነ ሲስት ግን የሚከሰተው ከ 55 ዓመት በላይ እድሜ የሚገኙ እናቶች ላይ መሆኑን አመላክተዋል ።

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review