የአፍሪካ ህብረት እና ሩሲያ በመርህ ላይ የተመሰረተ የሁለትዮሽ እና የባለብዙ ወገን የጋራ ትብብራቸውን ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር እና የአፍሪካ ህብረት ተወካይ ኢቭጌኒ ተረክሂንን በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።
ውይይቱ በአፍሪካ እና ሩሲያ ትብብር፣ በህዳር ወር 2018 ዓ.ም በሚካሄደው ሁለተኛው የሩሲያ- አፍሪካ የአጋርነት ፎረም የሚኒስትሮች ስብሰባ፣ በሳሄል ቀጣና ባሉ ጉዳዮች፣ የአፍሪካ ህብረት የሶማሊያ ሰላም ማስከበር ተልዕኮ እና የአቅም ግንባታ ኢኒሼቲቮች ላይ ያተኮረ ነው።
የአፍሪካ ህብረት እና ሩሲያ በብራዚል ቤለም የሚካሄደው 30ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባኤ(ኮፕ 30) የአፍሪካን የጋራ ድምጽ ለማጉላት የቅንጅት ስራቸውን ለማጠናከር ተስማምተዋል።
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ሩሲያ አፍሪካ በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና እንድታገኝ ድምጿን ማሰማትን ጨምሮ ለአህጉሪቷ አጀንዳዎች በመርህ ላይ ተመስርታ እያደረገች ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል።
አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት 80ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የአፍሪካ ቁልፍ ጉዳዮች በማስረጽ እና አህጉሪቷን በዓለም መድረክ ያላትን ውክልና ለማሳደግ ያደረጉትን ጠንካራ ተሳትፎ ማድነቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።