ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ እና በጎልደን ኮንኮርድ ግሩፕ የሚገነባው የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ መሠረት ድንጋይ ማስቀመጣቸውን በማህበራዊ የትስስር ገፃቸዉ ላይ አስፍረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ ዛሬ ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ የሚያኮራ ታሪካዊ ሁነት ተፈፅሟል። የሁለት አሻጋሪ ፕሮጀክቶች የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠናል ብለዋል።
የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ከሂላል የነዳጅ ስፍራ ድፍድፍ ነዳጅ በማውጣት፣ በማጣራትና በማጠራቀም በአመት 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን የማምረት አቅም አለው ሲሉም ነው የገለጹት።
በሌላ በኩልም የማዳበሪያ ፋብሪካው ከካሉብ የጋዝ ስፍራ በማውጣት እና 108 ኪሎ ሜትር የማጓጓዣ ቱቦ በመጠቀም በአመት 3 ሚሊዮን ቶን አምርቶ እንደሚያቀርብ ጠቅሰዋል።
እነዚህ ፕሮጀክቶች የኢንደስትሪ እድገትን ከማሳየት በላይ ናቸው በማለትም አክለዋል።
እድሎቻችንን የመጠቀም፣ ትብብሮችን የማጠናከር እና ሰላምን የማጽናት የጋራ ኃላፊነታችንን የሚያሳዩ ናቸውም ብለዋል።
በመሆኑም ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በኅብረት እና በአንድነት ለእድገት መሰባሰባችንን አጠናክረን እንድንቀጥል ጥሪ አቀርባለሁ ነው ያሉት።
ይኽን ስናደርግ እውነተኛውን የኢትዮጵያዊ ማንነት መንፈስ በሚያከብር መንገድ በአለም መድረክ የኢትዮጵያን ስፍራ ከፍ እናደርጋለን ሲሉ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው ላይ አስፍረዋል፡፡