ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መልእክት፤ በሶማሌ ክልል ካሉብ በአመት 111 ሚሊዮን ሊትር ማምረት የሚችለውን የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር መርቀናል ብለዋል።
በተመሳሳይም በአመት 1.33 ቢሊዮን ሊትር የማምረት አቅም የሚኖረውን ሁለተኛውን ዙር ማስጀመራቸውንም ገልፀዋል።
ከፈሳሽ ተፈጥሮ ጋዝ ምርት ባሻገር በኃይል ማመንጫ ዘርፉም 1000 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም በመያዝ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
ከሁሉም በላይ ፕሮጄክቱ የጋዝ ማምረቻ ብቻ አይደለም። ለማዳበሪያ ማምረቻ ወሳኝ የሆነውን ግብዓት በማቅረብ ለምግብ ሉዓላዊነት ጥረታችን የማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
ለኃይል ማመንጫ እና የክሪፕቶ-ማይኒንግ ሥራዎቻችን አስፈላጊ የሆኑ ግብዓቶችን ያቀርብልናል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል።
ዛሬ በሶማሌ ክልል የጀመርናቸው ከተያያዠ መሠረተ ልማቶች ግንባታ ጋር በአጠቃላይ ወደ 10 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው ሜጋ ፕሮጀክቶች በተገቢ ክትትል እስከ መጠናቀቂያቸው ይደርሳሉ።
የጀመርነውን ለመጨረስ ሁልጊዜም በጽናት እንደሠራነው ሁሉ ተጠናቀው ለአገልግሎት ይደርሳሉ ብለዋል።