“የመደመር መንግሥት” መፅሐፍ የሚነበብ ብቻ ሳይሆን የሚተገበር እና ከጽንፍ ተላቆ ወርቃማውን ማዕከል የመከተል እሳቤ የሚጠቁም መፅሐፍ መሆኑን ሙሁራን ተናግረዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ በተፃፈው “የመደመር መንግሥት” መጽሐፍ ዙሪያ በልደታ ክፍለ ከተማ የተዘጋጀ የፓናል ውይይት በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የልደታ ክፍለ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍትያለው ከፍያለው እና የልደታ ክፍለ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ም/ኃላፊ አቶ አሰፋ ቶላ የውይይት መድረኩን አስጀምረዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ ተጋባዥ እንግዶች በመፅሐፉ ላይ ያላቸውን ሙሁራዊ ግምገማ አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር)፣ የሶሽዮሎጂ ሙሁሩ ብርሃኑ ሌንጅሶ (ዶ/ር)፣ የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የሰላምና ደህንነት መምህሩ (ዶ/ር) ሙሉጌታ አየለ በመደመር መንግሥት መፅሀፍ ላይ ያላቸውን እይታና ይዘታዊ የዳሰሳ ትንተናቸውን አቅርበዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አራተኛ መጽሐፍ የሆነው “የመደመር መንግሥት” መፅሐፍ፣ ኢትዮጵያ ልትደርስበት ወደሚገባት ከፍታ ለመድረስ የሚያግዙ ቁልፍ ሀሳቦችን በቁጭት እንደሚያነሳ ገልፀው፣ ትውልዱ ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ በሀገራዊ ፍቅር እንዲነሳሳ መጽሐፉ ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው በውይይቱ ተመላክቷል።
“የመደመር መንግሥት” መፅሐፍ የሚነበብ ብቻ ሳይሆን የሚተገበር እንዲሁም ከጽንፍ ተላቆ ወርቃማውን ማዕከል የመከተል እሳቤ የሚጠቁም መፅሐፍ መሆኑንም ሙሁራኑ በመፅሀፍ ዳሰሳቸው ገልፀዋል።
መጽሐፍ ትናንት እና ዛሬን በጥልቀት በመፈተሽ ለኢትዮጵያ ብሩህ ነገ አመላካች የሆኑ ነጥቦችን የሚተነትን መሆኑን የጠቆሙት ተሳታፊዎቹ፣ የፓናል ውይይቱ ለብልጽግና መረጋገጥ መሠረት በሚሆኑ ሀሳቦች ዙሪያ ግንዛቤ እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
በውይይት መድረኩ የክፍለ ከተማና የወረዳዎች አመራሮች፣ ከክፍለ ከተማው የተውጣጡ ነዋሪዎች፣ አርቲስቶችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።
በይታያል አጥናፉ