የሰው ልጅ ከጥንት ስልጣኔ ጀምሮ ወርቅን ለክብር መግለጫ አለፍ ሲልም ለኑሮ ደረጃ መለኪያነት ሲያውለው ቆይቷል።
ከጥንት ጀምሮ እስከዛሬ ወርቅ ከጌጥነት ባለፈ የሀብት መለኪያ እና የክፉ ቀን መወጫ ሆኖ ቀጥሏል።
በብሔራዊ ባንኮቻቸው ውስጥ በርካታ ክምችት ያላቸው ሀገራት የገንዘባቸውን የመግዛት አቅም ለመወሰን ፤ብሎም ተለዋዋጭ በሆነው የአለም ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመዝለቅ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ ።
የወርቅ ክምችት (ጎልድ ሪዘርቭ) በየየሀገራቱ ማዕከላዊ ባንክ የሚቀመጥ የወርቅ መጠን ነው።
የወርቅ ክምችት ገንዘብ ለሚያስቀምጡ ሰዎች እንደዋስትና ሆኖም ያገለግላል።
በበርካታ ባህላዊና ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎች ላይ ከፍተኛ ቦታ ያለው ወርቅ በዓለማችን እጅግ አዋጭ የሚባለው የኢንቨስትመንት አይነት ነው።
የሰው ልጅ ከሚያወጣው ወርቅ ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው የሚገኘው ከምድር የላይኛው ክፍል ሲሆን ቀሪው ደግሞ ብዙ ርቀት ወደ ውስጥ ተቆፍሮ ነው የሚገኘው።
እንደ ዓለም የወርቅ ካውንስል መረጃ ከሆነ ከጥንት ስልጣኔዎች ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ የሰው ልጅ ወደ 216,265 ቶን የሚጠጋ ወርቅ
ከምድር ውስጥ ቆፍሮ አውጥቶ ለተለያዩ ተግባራት አውሎታል።
ከዚህ ውስጥ ወደ ሁለት ሶስተኛ የሚሆነው የተመረተው ከ1950ዎቹ ወዲህ ነው ፤ ይህ የሆነበት ምክንያት የማዕድን ማውጫ ቴክኖሎጂ መሻሻል እና አዳዲስ የወርቅ ክምችቶች በመገኘታቸው ነው።
የወርቅ ክምችት ያለበትን ቦታ ለማወቅ በሰላይነት ጭምር የታገዘ ፍለጋ የሚደረግ ሲሆን ወርቁን ከምድር ውስጥ ለማውጣትም ቢሆን ሮቦቶችን የሚጠቀሙ ድርጅቶች በርካታ ናቸው።
በዓለማችን ላይ እስካሁን ድረስ ከፍተኛው የሚባለው የወርቅ ክምችት የተገኘው በደቡብ አፍሪካ ‘ዊትዋተርስራንድ’ በሚባለው አካባቢ ነው ፤ የዓለማችን 30 በመቶ የወርቅ ምርትም ከዚህ ሰፍራ ለአለም ገበያ ቀርቧል።
በአሁኑ ሰአት ቻይና የዓለማችን ቁጥር አንድ የወርቅ አምራች ስትሆን እንደ ካናዳ፣ ሩሲያ እና ፔሩም ቢሆኑ ከፍተኛ አምራች ከሚባሉት ውስጥ የሚካተቱ መሆናቸውን የዓለም ወርቅ ካውንስል መረጃ ይጠቁማል።
ትሬዲንግ ኢኮኖሚክስ በ2025 በማዕከላዊ ባንኮቻቸው ከፍተኛ የወርቅ ክምችት ያላቸው ሀገራት ዝርዝርን ባወጣበት መረጃው፤ ከ8133 ቶን በላይ ወርቅ ያላትን አሜሪካ ቀዳሚ አድርጎታል ።
ጀርመን በ3352 ቶን ፣ ጣሊያን በ2452 ቶን ፣ ፈረንሳይ 2437 ቶን ወርቅ ክምችት ከሁለት እስከ አራት ያለውን ደረጃ ይዘዋል ።
በ2025 ከፍተኛ የወርቅ ክምችት ያላቸው የአለም ሀገራት ደረጃን ከስር ካለው ምስል ይመልከቱ ።
በዳዊት በሪሁን