በኢትዮጵያ የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ያለምንም ችግር እንዲከናወኑ የሀገርን ሰላምና ዳር ድንበር በማስጠበቅ ረገድ ሰራዊቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ነው

You are currently viewing በኢትዮጵያ የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ያለምንም ችግር እንዲከናወኑ የሀገርን ሰላምና ዳር ድንበር በማስጠበቅ ረገድ ሰራዊቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ነው

AMN መስከረም 23/2018

በኢትዮጵያ የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ያለምንም ችግር እንዲከናወኑ የሀገርን ሰላምና ዳር ድንበር በማስጠበቅ ረገድ ሰራዊቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑን በሀገር መከላከያ ሰራዊት የምስራቅ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ገለጹ።

ሌተናል ጄኔራል መሐመድ ተሰማ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ በሚገኘው በገርባሳ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ማዕከል ስልጠና ላይ ለሚገኙ የሰራዊቱ አባላት መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን በሐረር ቤተ መንግስት ሁለገብ አዳራሽ በመገኘትም በየደረጃው ካሉ የሰራዊቱ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

ሌተናል ጄኔራል መሐመድ በንግግራቸው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የሀገርን ሰላም ከማስከበር ባለፈ በሌሎች ሀገሮችም ከፍተኛ ስምና ዝና ያለው ጠንካራ ሰራዊት መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም በኢትዮጵያ የተጀመሩ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ግንባታ ያለምንም ችግር እንዲከናወኑ የሀገርን ሰላምና ዳር ድንበር በማስጠበቅ ረገድ ሰራዊቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶችና የውስጥ ባንዳዎች ጥምረት በመፍጠር ሀገር ለማፍረስ እየጣሩ መሆኑን ያነሱት ሌተናል ጄኔራሉ በሰራዊቱ ጀግንነትና ቁርጠኝነት በአስተማማኝ መልኩ እየተመከተ መሆኑን አንስተዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት ለመዳፈር የሚሞክር አካል ካለ ሰራዊቱ የላቀ ዝግጁነትና የተሟላ የመፈፀም አቅም ያለው መሆኑን አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ የጀመረችውን የከፍታ ጉዞ ለማሳካት የሰራዊቱን ባህርያትና እሴቶች በመላበስ በአመራሩ የተሰጡ ግዳጆችን በድል መወጣት ይገባል ብለዋል።

የምስራቅ ዕዝ ምክትል አዛዥ ሜጄር ጄኔራል ፍቃዱ ፀጋዬ፤ በበኩላቸው የኢትዮጵያን እድገትና ማንሰራራት እውን የሚያደርጉ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በተለያዩ አካባቢዎች በመገንባት ላይ መሆናቸውን አንስተው ምንም አይነት መስተጓጎል እንዳይገጥም ሰራዊቱ ሌት ከቀን መቆሙን ማረጋገጣቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በስልጠና ላይ የሚገኙ የሠራዊቱ አባላትም ለኢትዮጵያ ክብርና ሉዓላዊነት ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ ነን ብለዋል።

በሐረር ቤተ መንግስት በተካሄደው የውይይት መድረክም የሰራዊቱ አባላትና ከፍተኛ መኮንኖች ተሳትፈዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review