“የሀገራችንን ማንሠራራት ለማረጋገጥ በፈተናዎች ሳንበገር ተግተን እንስራ”

You are currently viewing “የሀገራችንን ማንሠራራት ለማረጋገጥ በፈተናዎች ሳንበገር ተግተን እንስራ”

                                                                                                                                                      ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

የአገራችንን ማንሠራራት ለማረጋገጥ በፈተናዎች ሳንበገር ተግተን እንስራ ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጠየቁ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ይህን ያሉት ለ2018 ዓ.ም የኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት መልዕክታቸው ሲሆን፣ የኢሬቻ እሴቶች የሆኑትን ሰላም፣ ምህረትና አንድነትን አጥብቀን በመያዝ የሀገራችንን ማንሠራራት ለማረጋገጥ በፈተናዎች ሳንበገር ተግተን እንድንሠራ አደራ ለማለት እወዳለሁ ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፣ ኢሬቻ የኦሮሞ የምስጋና ስርዓት መሆኑን ገልፀው፣ ኦሮሞ የሰው ዘር አፍርቶ የሚባዛው የተዘራው ሞቶ በመነሣት ፍሬ የሚያፈራው በፈጣሪ ድጋፍና እርዳታ ነው ብሎ ያምናል ብለዋል፡፡

ለዚህ ነው ኢሬቻ ሲደርስ ኦሮሞ ልበ ንፁህ የሆነውን ታላቅ ፈጣሪ ላደረገለት ሁሉ በማመስገን ለሚመጣው ጊዜ ደግሞ ምህረትን በመለመን ውዳሴ የሚያቀርበውም ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡

አክለውም፣ በጥንት የኦሮሞ ፍልስፍና ውስጥ ኦሮሞ ለውሃ ትልቅ ስፍራ አለው። ውሃ የንጽህና ምንጭ፣ የፍጥረትና የህይወት መሠረት ነው ብሎ ያምናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ ለዚህም ነው ሲፀልይ ፈጣሪ አምላክ፣ የፍጥረታት አምላክ፣ የቡርቃ ወላቡ (የወላቡ ምንጭ) አምላክ ብሎ ነው የሚፀልየው በማለት አብራርተዋል፡፡

የዘንድሮው ኢሬቻ ኢትዮጵያ የዜጎቿን የኢነርጂ ፍላጎት ለማሟላት የዓባይን ወንዝ በመገደብ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ባስመረቀችበት ማግስት የሚከበር መሆኑ ደስታችንን ድርብ ያደርገዋል ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አያይዘውም፣ ኦሮሞ መልካ የሌለው ህዝብ ራስ እንደሌለው ህዝብ ነው እንደሚል የባህር በር የሌላት ሀገር ኑሮ የሌላት ሀገር ናት ብለን ለህዝባችን ብልጽግና ስንል በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ የባህር በር ለማግኘት እየሠራን እንገኛለን ብለዋል፡፡

አክለውም፣ በዚህ ረገድ እያደረግን ያለነው እንቅስቃሴ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ተቀባይነት በማግኘት ላይ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት አዲስ እሳቤ በሆነው የመደመር ፍልስፍና በመመራት ሀገር ያላትን ሀብት፣ ልምድና እውቀት ከህዝባችን ጋር በመሆን ቁርጠኛና በሳል አመራር በመስጠት፣ ፈጣሪም አግዞን በበርካታ ችግሮች ውስጥ ሆነን አስደናቂ ለውጦችን አስመዝግበናል ሲሉም በመልዕክታቸው አመላክተዋል፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review