• የበዓሉ እሴቶች ኢትዮጵያ ወደ ልማት፣ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና ለመሸጋገር ለምታደርገው ጥረት ተምሳሌት መሆን እንደሚችል ተጠቁሟል

You are currently viewing   • የበዓሉ እሴቶች ኢትዮጵያ ወደ ልማት፣ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና ለመሸጋገር ለምታደርገው ጥረት ተምሳሌት መሆን እንደሚችል ተጠቁሟል

የኦሮሞ ህዝብ ዕለታዊ ህይወቱን፣ በሰው ልጅ መካከል፣ በሰውና አካባቢው፣ በፍጥረታትና ፈጣሪ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚመራበት ፍልስፍና አለው። ይህም በገዳ የአስተዳደር ስርዓት የሚገለፅ ሲሆን ለዘመናትም ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን ሲመራበት እንደኖረ የታሪክ ማስረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ዛሬና ነገ የገዳ ስርዓት አንድ አካል የሆነው ኢሬቻ በአዲስ አበባና ቢሾፍቱ ከተሞች በታላቅ ድምቀት ይከበራል። በኢሬቻ ሆረ ፊንፊኔ እና ሆረ አርሰዴ በዓላት በተለያዩ የሀገሪቱ ማዕዘናት የሚኖሩ የኦሮሞና የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች፣ በውጭ ሀገራት ጭምር የሚኖሩ ሰዎች ተሰባስበው “መሬሆ … መሬሆ…” እያሉ ፈጣሪን የሚያመሰግኑ ዜማዎችን እየዘመሩ፣ ሳርና አደይ አበባ በመያዝ ወደ መልካ (ወንዝ) በመውረድ ፈጣሪን ያመሰግናሉ። ሴቶችም ሲንቄ ይዘው፣ ጫጩ ደርበው፣ ጨሌ አድርገው፣ ለምለም ሳር ይዘው፣ በባህላዊ አልባሳት አጊጠው ከሌሎች የበዓሉ ተሳታፊዎችና አባገዳዎች ፊት በመሆን ይሄዳሉ፡፡

አቶ ከበደ አበራ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 አስኮ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ ናቸው፡፡ የኢሬቻ በዓል በጉጉት የሚጠብቁት በዓል እንደሆነና በየዓመቱ በሚከናወኑት የሆረ ፊንፊኔና ሆረ አርሰዴ ኢሬቻ በዓላት እንደሚሳተፉ ይናገራሉ፡፡ ብዙውን ጊዜም ከቤተሰብና ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ተመሳሳይ ቀለምና ዲዛይን ያላቸው ባህላዊ አልባሳት በመልበስ፣ ተውበውና ደምቀው፣ እየጨፈሩና እየተጫወቱ በደስታ ያከብራሉ፡፡

ኢሬቻ አስቸጋሪው የክረምት ወራት አልፈው በብራ፣ ወንዞች በሚጎድሉበትና ሰማዩ በሚጠራበት ወቅት የሚከናወን በዓል ነው፡፡ ሩቅ ቦታ የሚኖር፣ ሳይገናኝ የቆየ ቤተሰብ፣ ጓደኛና ወዳጅ ዘመድ መልካ (ወንዝ) ላይ የሚገናኙበትና ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርቡበት ትልቅ ደስታን የሚፈጥር በዓል እንደሆነ አቶ ከበደ ይገልጻሉ፡፡

ኢሬቻ ሰላም፣ ፍቅር፣ አንድነትና የህዝቦች አብሮነት የሚታይበት በዓል ነው፡፡ የኦሮሞ ህዝብ ከዓመት ወደ ዓመት ላሸጋገረው ፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት፣ ያለ እምነት፣ ዘር፣ ፆታና ሌሎች ልዩነቶች ሁሉም የሚሳተፍበትና የሚገናኝበት በዓል ነው፡፡ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችም የሚሳተፉበትና ወንድማማችነትና እህትማማችነትም የሚታይበት እንደሆነ አቶ ከበደ ያነሳሉ፡፡

“ኢትዮጵያውያን አውጥተን ብንጠቀማቸው ለሰላም፣ እርቅና ለልማት ተምሳሌት የሚሆኑ ባህሎች አሉን” የሚሉት አቶ ከበደ፣ በኢሬቻ በተለያዩ አካባቢ የሚኖሩ የኦሮሞ ማህበረሰብ፣ የተለያዩ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በፍቅርና በአንድነት በመሰባሰብ የሚያከብሩት በዓል መሆኑ ብዙ ቁምነገር ያስተምራል፡፡ አንድነት፣ መተባበርና ፍቅር ሲኖር የሚያስገኘውን ጠቀሜታ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ ኩራት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ሁነኛ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

አንድነት አሸናፊነት ነው፡፡ አያት ቅድመ አያቶቻችን ኢትዮጵያን ሊወር የመጣን ጠላት በአንድነት በመቆም አሸንፈዋል፡፡ የአሁኑ ትውልድ የህዳሴ ግድብን በመገንባት ዳግማዊ ዓድዋን ሰርቷል፡፡ በቀጣይም የጋራ የሚያደርጉንን ባህሎች በማክበርና በመጠበቅ እንዲሁም ከእነዚህ ትምህርት በመውሰድ የኢትዮጵያን አንድነት ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ የሚያቀራርቡንን እሴቶች በማውጣትና ለወጣቱ ትውልድ በማስተማር፣ በአንድነትና በፍቅር በመቆም በልማቱም ሆነ በሌላው መስክ አሸናፊ በመሆን ሀገርን ወደተሻለ ደረጃ ማድረስ ይቻላል፡፡ ከዚህ አኳያ እያንዳንዱ ጠንክሮ መስራትንና ሰላምን በማስቀደም መንቀሳቀስ እንዳለበት አቶ ከበደ ያስረዳሉ፡፡

የኢሬቻ በዓልን ከሚናፍቁና በየዓመቱ ተሳትፎ ከሚያደርጉት መካከል ሌላኛው የሳንሱሲ አካባቢ ነዋሪው አቶ ሽመልስ በቀለ ናቸው፡፡ በዓሉን ከቤተሰብና ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን በባህል አልባሳት አምረውና ደምቀው ያከብሩታል፡፡ በርካታ ሰዎች ከተለያየ አካባቢ የሚሰባሰቡበት በመሆኑ በቦታ ርቀት ለረጅም ጊዜ ሳያገኙአቸው የቆዩ ጓደኞቻቸው ጋር የሚገናኙበት፣ ከአዳዲስ ሰዎች ጋርም የሚተዋወቁበትና ወዳጅነት የሚመሰርቱበት፣ በጋራ ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት በዓል መሆኑም የተለየ ደስታ የሚፈጥርባቸውና በጉጉት እንዲጠብቁት እንደሚያደርጋቸው ይናገራሉ፡፡

ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ሰላምን፣ ፍቅርንና አብሮነትን የሚገልፅበት እንደሆነ የሚያነሱት አቶ ከበደ፣ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸው የሆነ የማንነት መገለጫዎችን ማወቅ፣ ማክበርና ማድነቅ ቢቻል ፍቅር፣ አንድነትና አብሮነት እየተጠናከረ ይሄዳል፡፡ የሀገሪቷን መልካም ገፅታ በመገንባት፣ የተለያዩ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች ያስገኛል፡፡

ኢሬቻና ተምሳሌትነቱ

ኢሬቻ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ እንደዘመን መለወጫ የሚታይ በዓል ነው፡፡ የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት ዋና ጸሀፊ እና የቱለማ አባ ገዳ ጎበና ሆላ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፤ ኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ከጨለማ ወደ ብርሃን በሚሸጋገርበት፤ የክረምቱ ጭጋግና ደመና ተገፍፎ፣ ሞልተው የነበሩት ወንዞችና ጅረቶች ጎድለው ሰዎች መገናኘት በሚችሉበት ወቅት የሚከበር እና ለፈጣሪ ምስጋና የሚቀርብበት በዓል ነው፡፡ በክረምት ከሚኖር ብርድ፣ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተትና ሌሎች አደጋዎች ታልፎ ወደ ብራ (ፀደይ) ላሸጋገረው፣ መሬቱ አረንጓዴ ሸማ በሚለብስበት፣ አበባ በሚያብብበት፣ አዝርዕት በሚያሽቱበት ወቅት ወደ መልካ (ወንዝ) በመውረድ ለፈጣሪ ምስጋና እና ልመና በማቅረብ በታላቅ ድምቀት የሚከበር ነው፡፡

“ከድቅድቅ ጨለማ ወደ ብርሃን፤ ከሌሊት ወደ ቀን፣ ከችግር ወደ ተስፋ ያሸጋገርከን፣ ከድፍርሱ ወደ ንጹህ ውሃ ያበቃኸን፣ አዝርዕትን ያበቅልክ፣ አበባዎች እንዲያብቡ ያደረክ፣ ያበበው እንዲያፈራ ተስፋ የሰጠኸን ፈጣሪ (ዋቃ) ምስጋና ይገባሃል” በማለት የሚመሰገንበት በዓል እንደሆነ የሚናገሩት ደግሞ በወለጋ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋዎችና ጥናት ተቋም ትምህርት ክፍል የተግባራዊ ሥነ ልሳን (የፎክሎር) መምህርና ተመራማሪ ግርማ በቀለ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ክረምት ወንዞች ከአፍ እስከ ገደፋቸው የሚሞሉበት፣ ድልድይ በውሃ የሚወሰድበትና የሚፈርስበት፣ ወዲህና ወዲያ ማዶ ያለ ወዳጅ ዘመድ የማይገናኝበት፣ ሀይለኛ ውሽንፍር፣ ጨለማ እንዲሁም ችግር ያለበት ወቅት ነው፡፡ ታዲያ ኢሬቻ ሲመጣ ዝናቡ በርቶ፣ ወንዞች ጎድለው፣ ጭጋጋማው አየር ተገፍፎ፣ ተለያይቶ የቆየው የሚገናኝበት፣ የሚጠያየቅበት፣ የሚመካከርበት፣ ወደ አንድነት የሚመጣበት፣ ተስፋ የሚሰነቅበት፣ ሰላምና ጤናን የሚመኝበት፣ መጪው ትውልድ በባህሉ የሚከናወነውን ወግና ስርዓት የሚማርበትን እድል እንደሚፈጠር ግርማ (ዶ/ር) ያነሳሉ፡፡

በኢሬቻ የኦሮሞ ህዝብ ከልጅ እስከ አዋቂ በመሰባሰብ፣ ‘መሬሆ … መሬሆ ’ እያለ በእጁ እርጥብ ሳርና አበባ በመያዝ ፈጣሪን እያመሰገነ ወደ ወንዝ ይወርዳል። ግርማ (ዶ/ር) እንደሚገልፁት፤ ኢሬቻ ሰላም፣ ፍቅር፣ ሀይል፣ አንድነት፣ መተባበር፣ እርቅ የሚታይበት በዓል ነው። በኢሬቻ ሰላም እንዲመጣና ያበበው እንዲያፈራ ለፈጣሪ ልመና ይቀርባል። የሚለመነውም በምድር ላይ ለሚኖር የሰው ልጅና ፍጥረታት ሁሉ ነው፡፡

መከፋፈል፣ መለያየትና ጥላቻ አይደገፍም፡፡ የኦሮሞ ህዝብ የራሱን ብቻ ሳይሆን ሌሎችን ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አቅፎ በመከባበርና በመደጋገፍ ይኖራል፤ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ያደርጋል፤ ያከብራል ይላሉ ግርማ (ዶ/ር)፡፡

እንደሀገርም ባለፉት ዓመታት ሰላም ለማምጣት ጥረቶች ተደርገዋል፡፡ በፌዴራል መንግስትና ህወሓት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት አንጻራዊ ሰላም የተፈጠረበትን ሁኔታ ማንሳት ይቻላል፡፡ ሰላም፣ መተባበር፣ አንድነት በመኖሩና ከልብ በመሰራቱ በተለያዩ የልማት መስኮችም በተጨባጭ የሚታዩና ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መገኘታቸውን ከሰላም አኳያ ያነሳሉ፡፡ 

ኢሬቻ የእርቅ ምልክትም ነው። የተጣላና ያኮረፈ ሰው ወደ ኢሬቻ አይሄድም፡፡ ምክንያቱም በኢሬቻ ወንዙ ሳይቀር ከድፍርስ ወደ ንጹህ መልክ የሚቀየርበት ስለሆነ፤ ሰውም በልቡ ቂም ቋጥሮ፣ የሻከረ ሀሳብ ይዞ ንፁህ ወደሆነው ወንዝ አይሄድም፤ በንፁህ ልብ ወደ ንጹህ ውሃ ነው የሚሄደው፡፡ ቂም ተይዞ ተስፋ አይሰነቅም፤ አንድነትም አይመሰረትም። የተጣሉ ወይም የተኳረፉ ወገኖች ሲታረቁ ባዶ እጃቸውን ሳይሆን እርጥብ ሳር ይዘው ወደ ወንዙ (መልካው) በመሄድ እንደሚያከብሩት ግርማ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡

ኢሬቻ ፍቅር የሚታይበትም በዓል ነው። ሰዎች በፍቅር ተሰባስበው፤ በመከባበር፣ በመደጋገፍና በአንድነት ፈጣሪያቸውን ይለምናሉ፡፡ ይህ የኢሬቻ እሴትም ኢትዮጵያ ወደ ልማት፣ ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና ለመሸጋገር የምታደርገው ጥረት ተምሳሌት መሆን እንደሚችል ግርማ (ዶ/ር) ያነሳሉ። “ኢሬቻ የሰላም፣ የምስጋና፣ የፍቅር፣ የአንድነት ተምሳሌት ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን የኢሬቻንም ሆነ ሌሎች በዓላትን እሴቶች መረዳትና ማክበር ቢችሉ ችግርም ሆነ ጦርነት አይኖርም፤ አንድነታችን ይጠናከራል፡፡ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባህልና እሴቶች አስተማሪ ናቸው፡፡” ይላሉ፡፡ 

ኢሬቻ ከጨለማ ወደ ብርሃንና ተስፋ የመሸጋገር ተምሳሌት ነው። ኢትዮጵያም ከድህነት ለመውጣት፤ ልማትና ብልፅግናን ለማምጣት በኢሬቻ የሚታየው የአንድነት እሴቶችን መያዝ ያስፈልጋታል፡፡ እዚህ ላይ አንድነት ሲባል አንድ አይነትነት ማለት ሳይሆን የተለያየ እምነት፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ የፖለቲካ አመለካከትና ክህሎት ያላቸው ሰዎች ለአንድ የጋራ ጉዳይ በጋራ መቆም ነው፡፡ እንደ ሀገርም ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሲቆሙና ሲተባበሩ ምን ማሳካት እንደሚችሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሚሰጠው ትምህርት ትልቅ እንደሆነ ግርማ (ዶ/ር) ያስረዳሉ። በዓባይ ወንዝ ላይ ልማት የማካሄድ የዘመናት ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ፣ ብሔር፣ ሃይማኖት፣ የፖለቲካ አመለካከትና ሌሎች ልዩነቶች ሳይገድቧቸው ገንዘብ በማዋጣት፣ በጉልበት፣ በሞራልና በዲፕሎማሲ ታይቶ የማይታወቅ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡

ሌላው ባለፉት ዓመታት በትኩረት የተሰራበትና ለውጥ የመጣበት የስንዴ ልማት ነው፡፡ ለዘመናት ኢትዮጵያ የስንዴ ፍላጎቷን የምታሟላው ከውጭ በመሸመት፣ በእርዳታና ልመና ነበር፡፡ ግርማ (ዶ/ር) እንደሚገልፁት፤ በስንዴ ልማት ህዝብን በሰፊው በማሳተፍ በመሰራቱ ከውጭ የሚሸመተውን ስንዴ ማስቀረት ተችሏል። ቀላል የማይባሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ህይወትም መቀየር ተችሏል፡፡

አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በኮሪደር ልማት ከተሞችን ለስራና ለኑሮ ምቹ እንዲሆኑ ለማድረግ በተደረጉ ጥረቶች ውጤት ማምጣት ተችሏል፡፡ የተለያዩ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ማከናወን ተችሏል፡፡

አዲስ አበባ፣ አርባምንጭ፣ ባህርዳር፣ ጎንደር፣ ሀዋሳና ሌሎች ከተሞችን ብናይ የዛሬ ሁለት ዓመት የሚያውቃቸው ሰው ዛሬ ቢያያቸው አያውቃቸውም፡፡ በኮሪደር ልማት ውብ፣ ፅዱና ለኑሮ ምቹ ሆነዋል። ይህም በቀን ብቻ ሳይሆን በሌሊትም ጨምር መስራት በመቻሉና የስራ ባህልን በመቀየር የተገኘ ነው፡፡ በየጊዜው እያደገ እንዲሄድ ቢደረግ ከዚህም በላይ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ግርማ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡

የፎክሎር መምህርና ተመራማሪው ግርማ (ዶ/ር) እንደሚገልፁት፤ ሰዎች ኢሬቻንና የተለያዩ በዓላትን በነቂስ ወጥተው በመሰባሰብ እንደሚያከብሩት ሁሉ፤ ለልማትና አንድነት እንዲነሳሱ ማቀድ ያስፈልጋል፡፡ የአንድ ሀገር ህዝቦች ከትንሽ እስከ ትልቅ ከተባበሩ፣ በአንድነት ከቆሙ፣ ያላቸውን ሀገር በቀል እውቀት፣ ክህሎትና አስተሳሰብ ካቀናጁ፣ ልክ እንደኢሬቻ በአደባባይ አውጥተው ሲጠቀሙና ሲተባበሩ በአንድ ሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤትና ለዓለም ሀገራት የሚጠቅም ስራ መስራት ይችላሉ። በመተባበር የማይለወጥ የነበረና የገዘፈ ችግር አይኖርም፡፡

ዘላቂ ሰላምን ከማረጋገጥ አኳያም ኢትዮጵያውያን ያለቻቸው “ኢትዮጵያ” የምትባል ሀገር ናት፡፡ ያለፈው ትውልድ በበጎም ሆነ በመጥፎ ሀገሪቱ አሁን ላለችበት ደረጃ የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል። አሁን ያለው ትውልድ ደግሞ የተሻለች ሀገር ለመፍጠር በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚና ፖለቲካው መስክ የሚታዩ ፈተናዎችን ለመሻገር ምክክርን ማስቀደም ይኖርበታል። ፍቅርና ምክክር ካለ ሰላም ይኖራል፡፡ ፍቅርና ሰላም ደግሞ ከቤት የሚጀምር በመሆኑ ሁሉም የድርሻውን መወጣት እንደሚጠበቅበት ግርማ (ዶ/ር) ያስገነዝባሉ፡፡

በኢሬቻ ከሰው ልጆች፣ እንስሳት፣ ዕፅዋት ጋር ሰላም መፍጠር ከፍተኛ ዋጋ ይሰጠዋል፡፡ ሰላምና እርቅም ከልብ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ተከፋፍለን መቆየታችን ልክ እንደ ክረምቱ ጨለማ የሚታይ ነው፡፡ በኢሬቻ ከጨለማ ወደ ብርሃን ሽግግር እንደሚደረግ ሁሉ በሀገራዊ ምክክርም ወደ አንድነትና ብሔራዊ መግባባትን ማምጣት ይቻላል፡፡ የሰላም፣ እርቅ፣ አንድነት መንፈስን በመያዝ ሀገራዊ ምክክር ማድረግ ከተቻለ ሀገራዊ መግባባት የማይፈጠርበት ምንም ምክንያት እንደማይኖር ግርማ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡ የሀገራዊ ምክክሩ ዓላማ ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነት፣ በሰላም፣ በአንድነት የሚኖሩባት ኢትዮጵያን መፍጠር ነው፡፡ ምክክርን ዋጋ ከሰጠነው በሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት ማምጣት እንደሚቻልም ያክላሉ፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review