የኢትዮጵያን ከፍታ ማሳያዎች

You are currently viewing የኢትዮጵያን ከፍታ ማሳያዎች

ህልማችን ሩቅ ነው፤ ተስፋችን የሚጨበጥ ነው

                                                                 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

የተመጣጠነ ልማት እኩልነትን ያፀናል፣ ሀገራዊ አንድነትን ያሳድጋል፣ ዕድገቱ ዘላቂና ሁሉን አቀፍ እንዲሆን ያደርጋል። ሀገራት በሁለንተናዊ መልኩ ጠንካራ ሆነው መቀጠል የሚችሉት ያላቸውን ሀብት በሚገባ ሲጠቀሙና ሁሉን አቀፍ የሆነ የኢኮኖሚ መንገድን መጠቀም ሲችሉ መሆኑን ከሃያ በላይ የፖለቲካል ኢኮኖሚ እና የፖለቲካል ርዕዮተ ዓለም የምርምር መፅሐፍትን ያሳተሙት ጀርመናዊው ኢኮኖሚስት አልበርት ኦቶ ሂርሽማን እ.ኤ.አ በ1958 “The Strategy of Economic Development” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መፅሐፍ ላይ አስፍረውታል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ይንገስ አለሙ (ዶ/ር) እንደሚሉትም ያደጉ ሀገራት የተከተሉት አዋጭ መንገድ ወደ ራስ መመልከትን፣ ያላቸውን ሀብት በሚገባ ማወቅን እና ከፍ ላለ ሀገራዊ ዕድገት መጠቀምን ነው፡፡ በዚህም አሜሪካ፣ ቻይና፣ ብራዚል፣ ጀርመን እና ሌሎቹም ሀገራት በኢኮኖሚ ከፍ ማለት ችለዋል፡፡ ኢኮኖሚ ደግሞ ሌሎቹንም መስኮች በበላይነት የመምራት ትልቅ አቅምን ይሰጣል፡፡

በመሆኑም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ሁሉንም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ያካለለ፣ ያለንን ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሀብት ያገናዘበ፣ ሀገርን በኢኮኖሚም ሆነ በሌሎች ዘርፎች ማላቅ የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ባሳለፍነው ረቡዕ መስከረም 21 ቀን 2018 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ተገኝተው በዓመት 111 ሚሊዮን ሊትር ማምረት የሚችለውን የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር ማስመረቃቸውን፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅን፣ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ ከተሞች እየተከናወኑ ያሉ ልማቶችን፣ ከመደበኛው መንገድ ባሻገር በበጋ መስኖ እየተመረተ ያለውን ስንዴ እና በሌሎች መስኮችም እየመጡ ያሉ ለውጦችን በዋቢነት በመጥቀስ ኢትዮጵያ በርግጥም ወደ ከፍታዋ ምዕራፍ እየተሻገረች ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሶማሌ ክልል የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ዙር ምርቃት፣ ሁለተኛ ዙር ማስጀመሪያ እንዲሁም የዩሪያ የአፈር ማዳበሪያ ፋብሪካ የመሰረተ ድንጋይ ማስቀመጣቸውን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልእክትም፣ “ዛሬ ለኢትዮጵያዊያን ሁሉ የሚያኮራ ታሪካዊ ሁነት ተፈፅሟል፤ የሁለት አሻጋሪ ፕሮጀክቶች የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠናል” ብለዋል፡፡

አክለውም፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመተባበር የሚገነባው የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካና በጎልደን ኮንኮርድ ግሩፕ የሚገነባው የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ የመሠረት ድንጋይ መቀመጡን ተናግረዋል፡፡

የኦጋዴን ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክት፣ የተመረቀው የመጀመሪያ ዙር በዓመት 111 ሚሊዮን ሊትር ማምረት የሚችል፣ የተጀመረው ሁለተኛ ዙር በዓመት 1 ነጥብ 33 ቢሊዮን ሊትር የማምረት አቅም ያለው ሲሆን፣ በሌላ በኩልም 1 ሺህ ሜጋ ዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ያለው መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት በይፋዊ ገፀ ድሩ ባሰፈረው መረጃ  ተመላክቷል፡፡

የጎዴ ነዳጅ ማጣሪያ ከሂላል የነዳጅ ስፍራ ድፍድፍ ነዳጅ በማውጣት፣ በማጣራትና በማጠራቀም በዓመት 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ቶን የማምረት አቅም እንዳለውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ጠቅሰዋል፡፡ በሌላ በኩል የማዳበሪያ ፋብሪካው ከካሉብ የጋዝ ስፍራ በማውጣት እና 108 ኪሎ ሜትር የማጓጓዣ ቱቦ በመጠቀም በዓመት 3 ሚሊዮን ቶን አምርቶ እንደሚያቀርብም ገልፀዋል፡፡

እነዚህ ፕሮጀክቶች የኢንዱስትሪ እድገትን ከማሳየት በላይ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እድሎቻችንን የመጠቀም፣ ትብብሮችን የማጠናከርና ሰላምን የማጽናት የጋራ ኃላፊነታችንን የሚያሳዩ መሆናቸውም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በህብረት እና በአንድነት ለእድገት መሰባሰባቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህን ስናደርግም እውነተኛውን የኢትዮጵያዊ ማንነት መንፈስ በሚያከብር መንገድ በዓለም መድረክ የኢትዮጵያን ሥፍራ ከፍ እናደርጋለን ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)።

“ህልማችን ሩቅ ነው፤ ተስፋችን የሚጨበጥ ነው፤ የገባንበትን ጥልቅ እንቅልፍ ህዳሴ በንጋት አንቅቶናል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ርዕያችን እንደ ኢትዮጵያዊ እና አፍሪካዊ ጠቃሚ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የተተከለ መሆኑን ማስታወስ  እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

በዚህ መንፈስ የሶማሌ ክልል መንግስት በቱሪዝም አዳዲስ እድሎችን እየከፈተ እንደሚገኝም ጠቅሰው፣ ወደ መጠናቀቂያ ምዕራፍ በደረሰው የገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ለምስራቁ የሀገራችን ክፍል አዲስ ዋጋ የጨመረ እድል እየፈጠረ መሆኑን ገልፀው፣ በአጠቃላይም የተመለከቱት የሥራ እድገት በጂግጂጋ እና በመላው ክልሉ የሚስተዋለውን መነቃቃት የሚያሳይ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

በርግጥም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተለያ ክልሎች ሰፊ መነቃቃቶች እየተፈጠሩ እና  ያልተነኩ አቅሞች ጭምር እየታዩ መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ። ለአብነትም ግብርና ሚኒስቴር ጥር 14 ቀን 2017 ዓ.ም ይፋ ባደረገው መረጃ መሰረት በፊት ጾሙን ሲያድር የነበረው ለም የአፋር ክልል መሬት በመስኖ ስንዴ ልማት ፕሮግራም አማካኝነት እየለማ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ በገፀ-ምድርና በከርሰ-ምድር ውሃ የታደለች እና ለመስኖ ምቹ ስነ-ምህዳር ቢኖራትም ግብርናው በተለይ ሰብል ልማቱ በዝናብ ላይ ጥገኛ ሆኖ መቆየቱ ለምግብ ዋስትናው ችግር እንደ አንዱ ምክንያት ሊጠቀስ ይችላል ይላል መረጃው፡፡

በሶማሌ ክልል የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ከዳንጎቴ ግሩፕ ጋር በመተባበር የሚገነባው የዩሪያ ማዳበሪያ ፋብሪካ መሰረተ ድንጋይ በተቀመጠበት ወቅት የዳንጎቴ ግሩፕ ባለቤት አሊኮ ዳንጎቴ ባስተላለፉት መልዕክት አሁን ላይ ኢትዮጵያ ኢንቨስተሮችን መሳብ የምትችል ሀገር ሆናለች፤ ለዚህም የሀገሪቱ መንግሥት ያደረገው ጥረት የሚደነቅ ነው ብለዋል።

በቅርቡ የተጠናቀቀው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመመረቁ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት አሊኮ ዳንጎቴ ግድቡን በራስ አቅም መገንባት መቻሉ እኛ አፍሪካውያን በራሳችን ምንም ነገር ማድረግ እንደማያቅተን ማሳያ መሆኑን መስክረዋል፡፡

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ይንገስ አለሙ (ዶ/ር) የዳንጎቴ ግሩፕ ባለቤት አሊኮ ዳንጎቴ ኢትዮጵያ ለአፍሪካ የመቻል ማሳያ መሆኗን መጥቀሳቸው ትክክል መሆኑን አንስተው፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ ልማቶች የሀገርን ከፍታ በፅኑ መሰረት ላይ የመገንባት የሚያስችሉና በርግጥም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሁለንተናዊ ተምሳሌት እየሆነች መምጣቷን የሚያመላክቱ መሆናቸውን እና ይህንንም ዓለም እያደነቀው ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

ጀርመናዊው ኢኮኖሚስት አልበርት ኦቶ ሂርሽማን እ.ኤ.አ በ1958 “The Strategy of Economic Development” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መፅሐፍ “ለምን ሚዛናዊ ልማት አስፈላጊ ሆነ?” ለሚለው ጥያቄ ቀጣዮቹን አበይት ነጥቦች ያነሳሉ፡፡ በሁሉም አካባቢዎች ያሉ ሀገራዊ ሀብቶችን በጥናት ላይ ተመስርቶ ለማልማት፣ ሚዛናዊ ልማትን ለማምጣት፣ በየአካባቢው ያሉ ያልተነኩ እምቅ ሀብቶችን ተጠቅሞ ሀገርን በፅኑ መሰረት ላይ ለመገንባትና ከፍ ለማድረግ ሁሉንም አካባቢዎች እና ሀብቶች ታሳቢ ያደረገ ሚዛናዊ ልማት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል፡፡

የተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ጥንካሬዎች እንዳሏቸው የጠቀሱት ጀርመናዊው ኢኮኖሚስት አልበርት ኦቶ ሂርሽማን ለአብነትም እንደ አካባቢው ሁኔታ ግብርና፣ ቱሪዝም፣ ማኑፋክቸሪንግ ወይም ዲጂታል ፈጠራን በማበረታታት እና በመጠቀም የሀገርን ሁለንተናዊ ከፍታ በአስተማማኝ መሰረት ላይ ለመገንባት ያግዛል ብለዋል፡፡

ለአብነትም ቻይና የባህር ዳርቻን ብልጽግና ከሌሎች አካባቢዎች ልማት ጋር ለማመጣጠን በዋና ዋና የመሠረተ ልማት ፕሮጄክቶችን በምዕራባዊ ክፍሎቿ ኢንቨስት በማድረግ እና ሁሉንም የሀገሪቱን አካባቢዎች አቅም በመለየትና በመጠቀም አሁን ላለችበት ከፍታ መሰረት እንደጣለች በዋቢነት ጠቅሰዋል፡፡

በሌላ በኩልም የህንድ ዕድገት ምንጭ ይኸው ሚዛናዊ ተሳትፎና ልማት መሆኑን የጠቀሱት ጀርመናዊው ኢኮኖሚስት፣ ህንድ ሁሉንም የሀገሪቱን ክፍሎች የሚያስተሳስሩ የኢንዱስትሪ ኮሪደሮችን ፈጠረች በዚህም ከፍታዋን ጨመረች፡፡ ብራዚልም ዕድገት ክልላዊ የማኑፋክቸሪንግ እና የከተማ ልማት ማበረታቻዎችን በማድረግና ምቹ አሰራርን በመፍጠር ሚዛናዊ ኢኮኖሚን በመገንባት መሰረት ያለው ዕድገት ማስመዝገቧን ጀርመናዊው ኢኮኖሚስት በመፅሐፋቸው አስፍረዋል፡፡

ካደጉ ሀገራት ልምድ በመነሳት ኢትዮጵያም እየተከተለች ያለው የኢኮኖሚ መስመር  እና እየተከናወኑ ያሉ ታላላቅ ልማቶችን ዋቢ በማድረግ  የኢትዮጵያን ከፍታ አይቀሬነት በርግጠኝነት መናገር እንደሚቻልም ከዝግጅት ክፍላችን ጋር ቆይታ ያደረጉት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር ይንገስ አለሙ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review