ቅርስ ያለፈውን መልካም ስኬትና እውነት ማስቀጠያ ድልድይ፣ ዛሬን ማጣፈጫ ቅመም፣ ለመጭው ትውልድ የምናስተላልፈው ቋሚና ሕይወት ያለው ሐውልት ነው፡፡ የቅርሶቻችን ምንጭ የሆኑት ባህልና ተፈጥሮ ደግሞ የማይተኩ የሰው ልጅ የመኖር አብነቶች ናቸውና ሊጠበቁ ይገባል፤ ይላል የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ቅርስን በዓለም አቀፍ ደረጃ መመዝገብና እውቅና መስጠት ለምን አስፈለገ ሲል በይፋዊ ገፀ ድሩ ባሰፈረው መረጃ፡፡
ዓለማችን በድንቃ ድንቅ ነገሮች የተሞላች የሰው ልጆች ውብ በረከት ናት። ከታሪካዊ ከተሞች፣ ቤተ መንግስቶች እና ካቴድራሎች እስከ አስደናቂ ተራሮች፣ የዝናብ መፍለቂያ ደኖች እና ውቅያኖሶች፣ በህብረ ቀለማት ያሸበረቁ ባህሎችን የመሳሰሉ ታላላቅ ሀብቶች የሰው ልጆች ሁሉ ናቸው።
ይሁን እንጂ የተፈጥሮ አደጋዎች፣ ጦርነቶች፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ቅርሶችን ታሳቢ ያላደረጉ ልዩ ልዩ ግንባታዎች እና መሰል አደጋዎች የቅርሶችን ሕልውና እየተፈታተኑት እንደሆነም በመረጃው ተመላክቷል፡፡
ይህንንም ተከትሎ በዓለማችን በየትኛውም ጥግ ያሉ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ክብርና ከፍታቸው ተጠብቆ ዓለም አቀፍ የሰው ልጆች ሁሉ ሀብት ይሆኑ ዘንድ ለመመዝገብና ለመጠበቅ እ.ኤ.አ 1972 የወጣውን የዩኔስኮ ኮንቬንሽን (የዓለም ቅርስ ስምምነትን) መሰረት በማድረግ 190 ሀገራት ስምምነቱን አፅድቀውታል፡፡
የዓለም ቅርስ ኮሚቴ በፓሪስ ባካሄደው 47ኛው ዓመታዊ ጉባኤ ዩኔስኮ 26 አዳዲስ የባህልና የተፈጥሮ ቦታዎችን በዓለም አቀፍ ቅርስነት መዝገብ ውስጥ አካቷል። ዩኔስኮ እ.ኤ.አ ሐምሌ 17 ቀን 2025 ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ መሰረት በ170 ሀገራት ያሉ 1 ሺህ 248 ቅርሶችን በዓለም ቅርስ መዝገብ አስፍሯል፡፡
የዩኔስኮ ዋና ዳይሬክተር ኦድሪ አዙሌይ የዓለም ቅርስ ኮሚቴ በፓሪስ ባካሄደው 47ኛው ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግርም “ቅርሶችን በዓለም ሀብትነት ማስመዝገብ ከብሔራዊ ድንበራቸው የተሻገሩ የባህላዊና የተፈጥሯዊ ፀጋዎች የሰው ልጆች ሁሉ ወካይ የሆኑ ልዩ ቅርሶችን የመጠበቅ እና የማስተዋወቅ ተግባር ነው” ብለዋል ።
ቅርስ አንድን ሀገር በየዘመናቱ ያለፈችባቸውን ስልጣኔ፣ ባህል፣ ወግ፣ ታሪክ፣ እሴት እና ማንነት ማሳያ ነው። ኢትዮጵያ ደግሞ የብዝሃነት አምባ በመሆኗ በርካታ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶች ባለቤት ናት፡፡ ቅርሶቿን በዩኔስኮ በማስመዝገብ በአፍሪካ ቀዳሚ ናት፡፡
በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት ከተመዘገቡ ቅርሶች መካከል የአክሱም ሐውልት፣ የላልይበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የመስቀል በዓል፣ የጌዴኦ መልክዓ ምድር፣ የኮንሶ የእርከን ስራ፣ የሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ የጎንደር ቤተ-መንግስት፣ የጢያ ትክል ድንጋይ፣ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ፣ የሐረር ጀጎል ግንብ፣ ፍቼ ጫምባላላ እና የገዳ ሥርዓትን መጥቀስ እንችላለን፡፡

የገዳ ስርዓት አካል የሆነውና ደማቅ ታሪክ፣ ማራኪ ውበት ያለው በተለይ ከአደባባይ በዓላት መካከል በርካታ ህዝብ የሚታደምበት ውበትና ፍቅር አብሮነትና ይቅርታ በህብረ ብሔራዊነት ደምቆ የሚታይበትን የኢሬቻ በዓል ራሱን ችሎ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ የተለያዩ ስራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የባህል ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደራራ ከተማ ይናገራሉ፡፡
አቶ ደራራ እንደሚሉት በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በየዓመቱ ለሁለት ጊዜ የሚከበረው የኢሬቻ በዓል የምስጋናና የእርቅ በዓል ተደርጎ ይወሰዳል። ኢሬቻ ከኦሮሞ ህዝብ ባሻገር የትኛውም የህብረተሰብ ክፍል የሚሳተፍበት የሰላምና አብሮነት ተምሳሌት የሆነ በዓል ነው፡፡
በዓሉ በህዝቦች መካከል መቀራረብን፣ ፍቅርንና እርቅን ለማምጣት የሚያግዝ እሴት ያለው በመሆኑ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ለማድረግ ለሁለት ዓመታት ያህል የፈጀ ጥናት እየተደረገ ሲሆን ኢሬቻ ካለው ድንቅ እሴት አንፃርም በዩኔስኮ መመዝገቡ አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡
ኢሬቻ የምስጋና ቀን ነው። ይህ በዓል በሁለት ቦታዎች እንደሚከበር የሚናገሩት አቶ ደራራ፣ ቦታዎቹም በሐይቆችና ወንዞች እንዲሁም በተራራዎች ላይ ነው። አንደኛው በክረምቱ መግቢያ ወቅት ላይ ሲሆን፣ ክረምቱን በሰላም አሻግረን፣ ውኃ እና እርጥቡን አትንሳን ተብሎ ፈጣሪን የሚለምኑበት፣ በተራሮች አናት ላይ የሚደረግ ነው። እርሱም ኢሬቻ ቱሉ ይባላል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ “ከክረምቱ አስፈሪ ነጎድጓድ እንኳን ወደ ብርሃን አወጣኸን። ብራውን ሰላም አድርግልን” በማለት በሐይቆችና ጅረቶች ዙሪያ ምስጋናን በማድረስ የሚከበር ነው። ኢሬቻ የመስማማትና የአንድነት በዓል ነው። የክረምቱን የጨለማ ወራት አልፈን ወደ ብርሃን የምንወጣበት ነው ተብሎም ምስጋና ይቀርብበታል፤ ደስታም ይገለጽበታል።
ኢሬቻ በዩኔስኮ መመዝገቡ እንደ ሀገር የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ደራራ፣ ኢሬቻ በክረምቱ ጎርፍና ጭጋግ አሊያም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ሰዎች በብዛት ከተለያየ ቦታ ተሰባስበው አንድ ቦታ ላይ የሚገናኙበት አጋጣሚ በመሆኑ የተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና መሰል ጥቅሞች አሉት፡፡ ለአብነትም ሰዎች ካሉበት ቦታ ተነስተው በዓሉን ለማክበር ወደ ማክበሪያ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ። በዚህ እንቅስቃሴያቸው ውስጥ ከመነሻቸው ጀምሮ እስከ መዳረሻቸው ለምግብ እና ለመጠጥ፣ ለመኝታ እንዲሁም ለተለያዩ አልባሳትና ጌጣጌጦች ወጪ ያወጣሉ። ይህም ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እንዲፈጥር የሚያስችል በዓል መሆኑን አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህም በላይ ልዩ የሚያደርገው ኢሬቻ ሁሉም ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ተወክለውበት የሚከበር አንድነትን የሚያጠናክር በዓል ነው፡፡ ይህንን የባህል መስተጋብር ለማየት የሚመጣው ዜጋ ቁጥርም ቀላል አይደለም፡፡
ይህንን ደማቅ የኢሬቻ በዓል ከገዳ ስርዓት ማሳያነት ባለፈ ራሱን ችሎ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ለማስመዝገብ በጥናት የተደገፈ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አቶ ደራራ ይናገራሉ፡፡
ዩኔስኮ በዓሉን ለማስመዝገብ የሚያስቀምጣቸውን መስፈርቶች ለሟሟላት የሚያስችሉ ጥናቶች እየተደረጉ መሆኑንም የሚናገሩት አቶ ደራራ ዩኔስኮ ከሚያስቀምጣቸው መስፈርቶች አንፃር እንደሚመዘገብ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ይቻላል ብለዋል፡፡
እንደ ዩኔስኮ መረጃ ከሆነ አንድን ቅርስ በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ያለው ጠቀሜታ፣ ዓለም አቀፍ እሴትነቱ፣ የተፈጥሮ ክስተት አሊያም ውበት፣ በዓለም ቅርስ ኮሚቴ በጂኦግራፊያዊ እና በታሪክ ተለይቶ የሚታወቅ እና መሰል መስፈርቶችን ያሟላ መሆን እንዳለበት ያስቀምጣል። ከዚህ አንፃርም ኢሬቻ የዩኔስኮን መስፈርቶች በሚገባ የሚያሟላ በመሆኑ መመዝገቡ አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡
አንድ ቅርስ በዩኔስኮ ከተመዘገበ በርካታ ጥቅሞች እንዳሉት የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ይፋ ያደረገው መረጃ ያትታል፡፡ ለአብነትም የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር የበለጠ ይጨምራል፣ ረዘም ላለ ጊዜ እንዲቆዩም ያደርጋቸዋል፤ ኢኮኖሚን ያነቃቃል፤ ከዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ፈንድ እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ለጋሾች ድጋፍ ያስገኛል፤ ለቅርሶቹ ጠንካራ የህግ ጥበቃ እና የፖሊሲ ድጋፍ እንዲኖር ያደርጋል፤ የማህበረሰቡን ተሳትፎና ማህበራዊ መስተጋብር የበለጠ ያጎለብታል፤ በሀገራት መካከል ጠንካራ መስተጋብር እንዲኖር እና ዓለም አቀፍ ገፅታን በተጠናከረ መልኩ ለማስተላለፍ ይረዳል።
በመለሰ ተሰጋ