“ዜጎች ላይ ምሬት የሚፈጥሩ አሰራሮችን ማስተካከል ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው”

You are currently viewing “ዜጎች ላይ ምሬት የሚፈጥሩ አሰራሮችን ማስተካከል ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው”

                        የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ

አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት የስማርት ከተማነት ጉዞን እንደሚያሳልጥ ተገልጿል

የዘመነና የተቀላጠፈ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት አንዱ የስልጡን ከተማ (ስማርት ሲቲ) መለያ መስፈርት ነው። አገልግሎት አሰጣጣቸውን ማዘመንና ማቀላጠፍ የቻሉ ከተሞች ያስቀመጡትን ርዕይ ለማሳካት አግዟቸዋል፡፡ በመዲናችን አዲስ አበባ በተግባር ሥራ የጀመረው አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት እንደ ሀገር ለተያዘው የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን የማዘመን ውጥን ወሳኝ ስንቅ ይሆናል፡፡

ዝግጅት ክፍላችን በቦታው ተገኝቶ ባደረገው ምልከታ በሰበሰበው መረጃ መሰረት፤ በዚህ ተቋም ሥራ ከመጀመሩ አስቀድሞ፤ የሀገር ፍቅር ስሜትን በመላበስ ሙያተኞች ዩኒፎርም ልብሳቸውን እንደለበሱ የኢትዮጵያ ህዝብን ብሔራዊ መዝሙር በመዘመር፣ ሠንደቅ ዓላማ የመስቀል ተግባርን በመደበኛነት ሁሌም ይፈፅማሉ፡፡ ከዚያም በሀገር ፍቅር መንፈስ፣ በብርቱ የሥራ ፍላጎት፣ በአገልጋይነት ወኔ ወደ ሥራቸው ይሰማራሉ፡፡ በግብዓትና በቴክኖሎጂ በተደራጀው የሥራ ክፍላቸው ገብተው፣ ከወንበራቸው ይሰየማሉ። ኮምፒዩተሮቻቸውን ከፍተውም ተገልጋዮችን እንዳመጣጣቸው በክብር ያስተናግዳሉ፡፡

አገልግሎቱ አስፈላጊ የሆኑ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች ተሞልተውለት፣ ለተገልጋይና ሠራተኛ ምቹ የሥራ አካባቢ ተመቻችቶለት እንዲሁም ብቁ የሰው ሃይል ተደራጅቶለት ጷጉሜን 5 ቀን 2017 ዓ.ም በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር  ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አማካኝነት ስራውን በይፋ ጀምሯል፡፡ ስለሚሰጡ አገልግሎቶች ማብራሪያ እና የተሟላ መረጃ የሚሰጠው የኤሌክትሮኒክስ የወረፋ መያዣ ወደየትኛው መስኮት መሄድ እንዳለብዎት ይጠቁምዎታል፡፡  ይህ ግር ካለዎት ደግሞ፤ አጋዥ የሠው ኃይል የፈለጉትን መረጃና ማብራሪያ ይሠጥዎታል፡፡

የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ ለዝግጅት ክፍላችን እንዳስረዱት፣ ዘመናዊ የመንግስት አገልግሎትን ለመገንባት ጠንካራና አዲስ የስራ ባህል መከተል ያስፈልጋል። አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት 13 ተቋማትን በማካተት፣ 107 የዲጂታል አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል እየሰጠ ይገኛል።

አዲስ መሶብ ምንድ ነው?

አዲስ መሶብ የአንድ መስኮት አገልግሎት በአንድ ጣራ ስር የተለያዩ የመንግስት አገልግሎቶችን በማጣመርና የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሚሰጥ አገልግሎት ስለመሆኑ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ዮናስ ተናግረዋል። “የአሠራር ስርዓቱ ዜጎች የዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም በቀላሉ የተለያዩ የተቋማትን አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል ነው፡፡ በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ በተለይ ዜጎች ላይ ምሬት የሚፈጥሩ አሰራሮችን ፈትሾ ማስተካከል ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው። ለዚህ ቁርጠኝነታችን አንዱ ማሳያ የሆነው የአዲስ መሶብ የአንድ መስኮት አገልግሎት ደግሞ የመዲናዋን ነዋሪ ችግር የሚቀርፍ ነው፡፡ በተለይም ባለጉዳዮች ወደተለያዩ ቢሮዎች የሚያደርጉትን ምልልስ፣ ረጅም የወረፋ ጥበቃ እና ከወረቀት ጋር ተዛማጅ የሆኑ ስራዎችን የሚያስቀር ነው” ብለዋል።

በአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ውስጥ 13 ተቋማት ማለትም ንግድ ቢሮ፣ ገቢዎች ቢሮ፣ ስራ እና ክህሎት ቢሮ፣ መሬት ልማት እና አስተዳደር ቢሮ፣ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ፣ ፕላን እና ልማት ቢሮ፣ የመሬት ይዞታ ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ፣ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ፣ የግንባታ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የቤቶች ኮርፖሬሽን፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን፣ የአሽከርካሪ እና ተሽከርካሪ ፈቃድ እና ቁጥጥር ባለስልጣን፣ የትራፊክ ማናጅመንት ባለስልጣን ተካትተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከክፍያ አኳያ የሚያግዙ እንደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ስኬት ባንክ፣  የኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት፣ የብሔራዊ መታወቂያ እንዲሁም የሰነዶች ማረጋገጫ እና ምዝገባ አገልግሎት እንደሚገኙበት አቶ ዮናስ ገልፀዋል፡፡

ይህ አገልግሎት የአዲስ አበባን የስማርት ከተማነት ጉዞ የሚያሳልጥ ወይም የሚያግዝ ነው፡፡ “የአዲስ አበባ ስማርት ሲቲ ዕቅድ” ጥናት ተጠንቶ ወደ ትግበራ ከገባ ሰነባብቷል፡፡ ይህ ዕቅድ በውስጡ ካካተታቸው የስማርት ሲቲ ስድስት ዋና ዋና ምሰሶዎች መካከል አንዱ ስማርት ገቨርናንስ (ስማርት የመንግስት አገልግሎት) ነው፡፡ ይህንን አስመልክቶ በወቅቱ በጥናቱ ላይ የተሳተፉት በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር፤ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስና ሮቦቲክስ ልህቀት ማዕከል ኃላፊ የነበሩት ቱሉ ጥላሁን (ዶ/ር) ከአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳብራሩት፤ ስማርት ገቨርናንስ (ስማርት የመንግስት አገልግሎት) ማለት፤ ነዋሪዎች የሚያገኟቸውን የመንግስት አገልግሎቶች ፈጣንና ቀልጣፋ ማድረግን የሚመለከት ነው፡፡ ተገቢውን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሰልፍን መቀነስ፣ ከሰው ንክኪ ውጪ አገልግሎት በመስጠት ግልጽነትን መፍጠርና ብልሹ አሰራርን ማስቀረትን ዓላማው ያደረገ ነው፡፡

ከአደረጃጀት አንፃር የተደረገው ዝግጅት

 “አዲስ የአገልግሎት አድማስ” በሚል መሪ ሀሳብ በአደረጃጀት፣ በአሠራር ስርዓት እንዲሁም በሠራተኛ ስነ ምግባር ጠንከር ያለ ቆራጥ አቋም በመያዝ ወደ ሥራ መገባቱን የሚናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ሠራተኞች በሥራ ቦታቸው ላይ ሆነው በተለያየ ነገር ሃሳባቸው እንዳይሰረቅ ብሎም ለብልሹ አሠራር ተጋላጭ እንዳይሆኑ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን ይዘው ወደ ሥራ ክፍላቸው አይገቡም፡፡  ከዚህ ቀደም በሀገራችን ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ይነሱ የነበሩ ክፍተቶች እንዲታረሙ እና በዚህ ማዕከል እንዳይደገሙ በማዕከሉ የተዘረጋው የአሠራር ስርዓት ሁነኛ መፍትሔ እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡ በሠራተኛ የሥራ ስነ ምግባር ላይ ተጠባቂው ውጤት እንዲመጣ፤ ሠራተኞች ወደ ሥራ ከመግባታቸው አስቀድሞ ለ15 ቀናት በኢትዮጵያ አቬይሽን ዩኒቨርሲቲ ስልጠና ወስደዋል፡፡ ስለማዕከሉ የሥራ ስነ ምግባርም በጥልቀት ገለጻ እና ማብራሪያ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

በቃሉ ታደሰ ይባላል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ የትምህርት ዘርፍ በ2017 ዓ.ም ተመርቋል። በአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት የሲቪል ምዝገባ እና ነዋሪዎች አገልግሎት ኤጀንሲ ውስጥ ባለሙያ ነው፡፡ የልደት ሰርተፍኬት፣ የሞት ምዝገባ፣ ጋብቻ፣ ጉዲፈቻ እና ፍቺ መሰል አገልግሎቶችን በአዲስ መሶብ ይሰጣል፡፡ ወደ ሥራ ከመግባቱ በፊት ከደንበኞች አልያም ከባለጉዳዮች ጋር ሊኖረው ስለሚገባ ግንኙነት በቂ ስልጠና አግኝቷል፡፡ ሙያውንም በተመለከተ እንዲሁ የስራው ባህሪ ላይ  ምን እንደሚመስል ጭምር አውቆ ወደ ሥራ ስለመግባቱ ተናግሯል፡፡

ሰዎች አለአግባብ ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውንና ገንዘባቸውን እንዳያባክኑ የዘመኑ የአሠራር ስልቶችን ተግባራዊ ማድረግ ወሳኝ ሚና እንዳለው የሚናገረው ደግሞ በአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ውስጥ ሁሉን አቀፍ አገልግሎት ሰጪ ባለሙያ አዲሱ ፈንቴ ነው፡፡ “ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ማዕከል ማግኘት መቻል መጉላላቶችን ብሎም አላስፈላጊ ትርምሶችን የሚቀንስ ነው፡፡” ሲል ገልጿል፡፡

ይህን ሀሳብ በማዕከሉ ያገኘናቸው ተገልጋዮችም ያጠናክሩታል፡፡ ወጣት መንግስቱ ተስፋው፤ ነዋሪነቱ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ነው፡፡ የፋይዳ መታወቂያ ለማውጣት ወደ አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የመጣ ሲሆን፤ ቀልጣፋ እና ምቹ የአሠራር ስርዓት በተቋሙ ስለማግኘቱ ተናግሯል። ማህበረሰቡን ለምሬትና ለእንግልት የሚዳርጉ የአሰራር ስርዓቶችን አስቀርቶ የከተማን እድገት ለማፋጠን መሰል ሁነኛ መላዎችን ማስፋት ያስፈልጋል ሲልም አክሏል፡፡

የተለያዩ ጉዳዮችን በፍጥነት ለማስፈፀም እንሰራለን የሚሉ ህገ ወጥ ደላሎች እጃቸውን እንዳያስገቡ ብሎም ከተቋሙ ሰራተኞች ጋር ፍፁም ግንኙነት እንዳይፈጥሩ  ማስቻል ከማዕከሉ የሚጠበቅ እንደሆነ የጠቆሙት የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ፤ ለዚህ የሠራተኛውን ግንዛቤ የማሳደግ፣ የሥራ ላይ ስነ ምግባር መርህና ህግን የማሳወቅ እንዲሁም በቴክኖሎጂ የታገዘ ክትትል የማድረግ ስራ ከተከናወኑት መካከል እንደሚጠቀሱ አብራርተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፤ በማዕከሉ በሆነ አግባብ ከተማዋን በሚመስል የሰው ሃይል ተደራጅቷል፡፡ አዲስ እና ነባር ሠራተኞችን ያካተተም ነው፡፡ የሠራተኞች ስብጥርን በተመለከተ ብቃታቸውን በምዘና በማረጋገጥ ከየተቋማቱ ነባር ሠራተኞች ወደማዕከሉ እንዲቀላቀሉ ተደርገዋል፡፡ ጥሩ ውጤት ያላቸውን አዲስ ምሩቅ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በመፈተን አብላጫ ውጤት ያመጡትን ወደ ሥራ ለማስገባት ስለመቻሉም ገልፀዋል።

የማዕከሉ ሠራተኞች ሥራ ከመጀመራቸው አስቀድሞ የወሰዷቸው የስልጠና ኮርሶች አካዳሚው ለአየር መንገድ እና ሌሎች የደንበኛ ተኮር ዘርፎች የሚሰጠውን ዓለም አቀፍ ስታንዳርድ የጠበቀ ስልጠና ስለመሆኑ አቶ ዮናስ ገልፀዋል፡፡ አያይዘውም መስሪያ ቤቱ የሰራተኛ ስነ- ምግባርን በተመለከተ ጥብቅ የሆነ መመሪያ ያዘጋጀ ሲሆን ሰራተኞቹ ተቋሙን ከመቀላቀላቸው አስቀድሞ እጅግ ጥብቅ በሆነው የደንብ ልብስ አለባበስ እና የስራ ቦታ ህግጋቶች ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተደርጓል። ይህን መሰል የአሰራር ስርዓት ለመከተል ምክንያት የሆነው ደግሞ የተገልጋይ እርካታን ለማሳደግ ብሎም ከዚህ ቀደም የነበረውን ችግር ለመቅረፍ በማሰብ ጭምር ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡

በወረዳ እና በክፍለ ከተማ የሚሰጡ አገልግሎቶች እንደተጠበቁ ሆኖ አንድ እና ከዚያ በላይ የተሳሰሩ አገልግሎቶችን ማግኘት የሚፈልግ ሰው አዲስ መሶብ ላይ መገልገል ይችላል፡፡ ከአንድ ተቋም ወደ ሌላ ተቋም አካባቢ ቀይሮ ከመንቀሳቀስ ይልቅ አንድ ቦታ አገልግሎቱን እንዲያገኝ የሚያስችል ነው፡፡ ተደራሽነትን ከማስፋት አንፃርም በርካታ ስራዎችን ለመስራት እንደታሰበ የሚገልጹት አቶ ዮናስ፣ በማዕከል ደረጃ ያለው የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ዋና መስሪያ ቤት ነው፡፡ ከሰሞኑ የቦሌ አዲስ መሶብ ቅርንጫፍ በይፋ ስራ ይጀምራል፡፡ በበጀት ዓመቱ በሁሉም ክፍለ ከተሞች አማካኝ በሆነ ቦታ ላይ የመሶብ አገልግሎት ለመጀመርም እቅድ አለ፡፡ ከ13ቱ ተቋማት በተጨማሪ ሌሎች አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ ለመስጠት ብቁ የሆኑትን ለማካታተም መታሰቡን ተናግረዋል፡፡

በሄለን ጥላሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review