ለኪነ ጥበባዊ ፈጠራ ዕድል የሚሰጠው በዓል

You are currently viewing ለኪነ ጥበባዊ ፈጠራ ዕድል የሚሰጠው በዓል

 • ኢሬቻ መነሻው ይቅር መባባል፣ ፈጣሪን ማመስገንና ከተፈጥሮ ጋር መስተጋብር መፍጠር በመሆኑ ለኪነ ጥበባዊ ፈጠራዎች ትልቅ መነሻ እንደሆነ ተገልጿል

ወርሃ መስከረም ተፈጥሮ ውበቷን የምትገልጽበት እና ራሷን አጉልታ የምታንጸባርቅበት ወቅት ነው፡፡ የደፈረሱ ወንዞች በመስከረም ይጠራሉ፡፡ ጭጋግ የሸፈናቸው መስኮች በመስከረም ፀአዳ አረንጓዴ ይለብሳሉ፡፡ ምድር በአበቦች ታጌጣለች፡፡  ሰማይ ነጭና ሃምራዊ ልብሷን አገልድማ ትታያለች፡፡

በመስከረም ፈገግ የምትለው ተፈጥሮ፣ ፈገግታዋ ወደ ሰውም ይጋባል፡፡ ይህቺ ተፈጥሮ በሰው ልብ ውስጥም ተስፋን ትጭራለች፡፡ አዲስ ዕይታና አዲስ መሻትን ትፈነጥቃለች። አሮጌውን በመሸኘት የአዲስ ዘመን መምጣትን ታውጃለች፡፡ ተራርቀው የቆዩ ቤተ-ዘመዶችን በማገናኘት፤ የተነፋፈቁ ወዳጆች ናፍቆታቸውን እንዲወጡ ዕድል ታመቻቻለች፡፡

የመስከረም ወር ልዩ ነች፡፡ ተፈጥሮ ዳግም የሚታደስባት፣ ብዙ አይነት ተፈጥሯዊ ቀለሞች የሚታዩባት ናት። በዚሁ ወር የሚከበረው ኢሬቻም ከተፈጥሮ እና ከማህበረሰቡ ህይወት ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ኢሬቻና በዓሉ የሚከበርበት ወቅት በራሱ ተፈጥሮን፣ ህይወትን፣ ባህልንና ታሪክን መሰረት አድርገው ለሚጠበቡ ከያኒያን ትልቅ መነሳሳትን ይፈጥራል። በዚህ አጭር ዓምድም የኢሬቻ ዕሴቶች ለኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎች ያላቸው ዕምቅ አቅምና ከያኒያን ይህን ዕሴት በጥበብ ስራዎቻቸው እንዴት ማንጸባረቅ እንደሚችሉ በጨረፍታ ልናስቃኛችሁ ወድደናል፡፡

ኢሬቻን በጨረፍታ

በኦሮሞ ባህል ጥናት ውስጥ ተመራማሪ የሆኑት መምህር ጌታቸው አበራ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት፣ የኢሬቻ በዓል የመልካም ነገሮች ሁሉ ምንጭ ለሆነው ለፈጣሪ ምስጋና የሚሰጥበት ቀን ነው። በዚህ ቀን ሕዝቡ  ለተደረጉለት መልካም ነገሮች ሁሉ ከልብ የመነጨ ምስጋና ለፈጣሪው ያቀርባል። የተጣሉ ሰዎች እርቅ ያደርጋሉ፡፡ ከዚህ አንጻር በዓሉ የሰላም፣ የፍቅርና የእርስ በእርስ ትስስራችንን የምናጠናክርበት ነው ብለዋል፡፡

በሃሮማያ ዩኒቨርስቲ የታሪክ ተመራማሪ መሐመድ ሐሰን (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም ለአዲስ ልሳን ዝግጅት ክፍል በሰጡት አስተያየት፣ ኢሬቻ የሚከበርበት ምክንያት፣ በክረምት ዝናብና የወንዝ ሙላት ተለያይተው የከረሙ ቤተሰቦች የሚገናኙበት እና ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት ወቅት በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡

እንደ  መሐመድ (ዶ/ር) ገለጻ፣ ኢሬቻን በቂምና በጥላቻ ሳይሆን፣ ይቅር በመባባል እና በንፁህ ልብ የሚከበር ነው፡፡ የሰላም፣ የፍቅር፣ የደስታ፣ የህብረትና የአንድነት በዓል ነው፡፡ ቡቃያው አሽቶ፣ ጎምርቶና አዝመራው ደረስኩ ደረስኩ የሚልበት ወቅት ስለሚከበር የተስፋ ጊዜ ነው፡፡

መሐመድ (ዶ/ር) አክለውም፤ “ኢሬቻም ሆነ ሌሎች የአደባባይ በዓላት በባህርያቸው ዜጎችን በአንድ መድረክ የሚያሰባስቡ ናቸው፡፡ ዜጎች በዓሉን ለማክበር በአንድ መድረክ ላይ ሲገናኙ ይበልጥ መገነዛዘብ ይጀምራሉ። የባህል ልውውጥ ከማድረጋቸውም በላይ ኢትዮጵያ በተለያዩ ባህሎች ያሸበረቀች ውብ ሀገር መሆኗን ይረዳሉ። ይሄ ደግሞ በሂደት ይበልጥ የእኔነትን ስሜት አዳብረው፣ በሀገራቸው ባህሎች መኩራት ይጀምራሉ፡፡ ይህ ማለት ሰሜን ውስጥ ያለውን ባህል ደቡብ፤ ደቡብ ውስጥ ያለውንም ደግሞ ሰሜኑ የበለጠ ያውቀዋል፡፡ ልክ እንደዚሁ ምስራቅ ውስጥ ያለው ባህል ምዕራቡ፤ ምዕራብ ውስጥ ያለው ደግሞ የምስራቁ የበለጠ ይገነዘበዋል፡፡ ይሄ ደግሞ በሂደት የእርስ በእርስ ትስስርን ያጎለብታል፡፡ አብሮነትን ያሳድጋል፡፡ ከዚህም አልፎ በሂደት መሰል በዓላት ለማሳደግ እያንዳንዱ ዜጋ ሃላፊነቱን ለመወጣት በራሱ ተነሳሽነት ዕገዛ ያደርጋል” ብለዋል፡፡

ኢሬቻና ኪነ ጥበብ

የኢሬቻ በዓል መነሻው ይቅር መባባል፣ ፈጣሪን ማመስገንና ከተፈጥሮ ጋር መስተጋብር መፍጠር በመሆኑ ኪነ ጥበባዊ ለሆኑ የፈጠራ ሥራዎች ትልቅ መነሻ ነው፡፡ ከያኒያን የማህበረሰቡ አንድ አካል በመሆናቸው፣ ማህበራዊ ጉዳዮችን ይመለከታቸዋል፡፡ በዚህ ምክንያት የባህል ዕሴቶች የፈጠራ ሥራቸው አካል አድርገው ለመጠቀም ያስችላቸዋል፡፡ 

በኢሬቻ ሰሞን ብርሃናማ ቀለሞች በብዛት ይታያሉ፤ አደይ አበባ በመስኩ እና በጋራው ላይ ይፈካል። የሰው አለባበስም በቀለምና ጥበብ ያሸበረቀና የደመቀ ይሆናል፡፡ ወንዞች ንጹህ ይሆናሉ፡፡ በዙሪያችን የምናየው ሁሉም ነገር ውብ እና የተለያየ ቀለም ያለው ነው። በመሆኑም የኢሬቻ በዓል አከባበርና የተፈጥሮ ሁኔታ ለከያኒያን ለጥበባዊ ፈጠራቸው መነሻ መሆን ይችላል፡፡

መምህር ጌታቸው በማብራሪያቸው፣ “ኢሬቻን በብዙ መልኩ ሊገለጹ የሚችሉ እሴቶች አሉት፡፡ የኪነ ጥበብ ሰዎችም የበዓሉን መልከ ብዙ እሴቶችና ፋይዳዎች በኪነ ጥበባዊ ሥራዎቻቸው አጉልተው ለማሳየት ምቹ ነው፡፡ ለአብነትም አንድ ዲዛይነር የሆነ ሰው፣ የኢሬቻን መልከ ብዙ እሴቶችን የሚያሳዩ የአልባሳት ዲዛይኖችን መስራት እንደሚችል ሁሉ በዓል ሲከበር ያለው ድባብም ለጥበብ ሰዎች የፈጠራ ስራ ትልቅ መነሻ መሆን ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በ“ሪያሊዝም” የአሳሳል ዘይቤ  የሚታወቀው ሰዓሊ ግርማ ቡልቲ ኢሬቻን በኪነ ጥበባዊ ስራዎች ማሳየት የቻለ ከያኒ ነው፡፡ ሰዓሊ ግርማ ከተማሪነቱ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ኢሬቻን የተመለከቱ በርከት ያሉ የስእል ስራዎችን አበርክቷል። የሳላቸውን ስዕሎችም ለዕይታ ማብቃት ችሏል፡፡ የባለፈው ዓመት የኢሬቻ በዓል ለእይታ በቅቶ በነበረው የሥዕል አውደርእይ ላይም አዳዲስ ስራዎችን አቅርቧል፡፡ ስራዎቹም በብዛት ባህል፣ መተሳሰብ፣ ይቅርታ፣ ፍቅር፣ ሰላምና የማህበረሰቡ አጠቃላይ መስተጋብር ላይ የሚያጠነጥኑ ናቸው፡፡ ሰዓሊ ግርማ፤ በኢሬቻ ሰሞን ልዩ አይነት ቀለም፣ ባህል፣ ተፈጥሮ፣ አለባበስ እና ሌሎች ሁነቶች ስለሚታዩ ዕውናዊ የአሳሳል ዘይቤ “Realism Painting” ላይ ትኩረታቸውን አድርገው ለሚሰሩ ሰዓሊያን እና ለሌሎችም ከያኒያን ትልቅ የሃሳብ ምንጭ አድርገው ሊጠቀሙት እንደሚችሉ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግሯል፡፡

ሰዓሊ ግርማ በገለጻው፣ እንደ ኢሬቻ ያሉ በዓላት፣ ባህላዊ እና ታሪካዊ የስእል ስራዎች ሲሰሩ ጥናቶች ተደርገው ነው። ጥናቱ ደግሞ ማህበረሰቡን ሙሉ በሙሉ የሚገልጽ መሆን አለበት። ለዚህም ቦታው ላይ በመሄድ ጥናት በሚሰራበት ጊዜ ምእናባዊውን ሳይሆን እውነተኛውን መልክአዐ ምድር፣ የማህበረሰቡን አለባበስ፣ አመጋገብ፣ በዓል አከባበርና የእለት ተእለት አኗኗር መረዳት ይቻላል፡፡

መምህር ጌታቸውም የሰዓሊ ግርማን ሃሳብ የሚያጠናክር አስተያየት ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡ የኢሬቻን መልክ ብዙ ሀገራዊ ፋይዳዎቹን በመገንዘብ ጥናቶች እየተደረጉ ነው ያሉት መምህር ጌታቸው፣ ለኪነ ጥበባዊ የፈጠራ ሥራዎችና የጥበብ ሰዎች መነሻ ሊሆን የሚችል “ኢሬቻ” የተሰኘ መጽሐፍ በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ተጽፎና በጥናት ማዕከሉ አማካይነት ታትሞ ለንባብ በቅቷል፡፡ መጽሐፉን በቀጣይ በአማርኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች አሳትሞ ለተደራሲያን ለማቅረብ ታቅዷል፡፡ ይሄ አይነት የምርምር ስራዎች ማድረግና ማሳተም ኪነ ጥበብን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎችም ይቀጥላል ብለዋል፡፡

በኢሬቻ ጊዜ በተለይ በገጠራማ አካባቢዎች የማይለበስ የልብስ አይነት የለም፡፡ ሁሉም ሰው በተለይ በኦሮሚያ ክልል ለበዓሉ ብሎ የሚሰራ ልብስ አለ። በዚህ ልብስ ላይ የሚታዩ ጥበቦችና ቀለሞች በጣም ማራኪ ናቸው፡፡ እነዚህ አልባሳት በራሳቸው ለጥበባዊ ስራዎች መነሻ ናቸው፡፡

ከአልባሳት ባለፈ ዝግጅቱ የሚከበርበት መልካ ወይም ወንዝ አለ። ኢሬቻ መልካ የሚከበረው በወንዝ ዳርቻ ነው። የበጋው ኢሬቻ ወይም ኢሬቻ ቱሉ ደግሞ በተራራ ላይ የሚከበር ነው፡፡ ሁለቱም አንድ የሚያደርጋቸው የምስጋና ቀን መሆናቸው ነው፡፡ ይህ አጋጣሚ ለጥበብ ሰዎች የበዓሉን አከባበር፣ ድባብና በዓሉ የሚከበርበት አካባቢ ተፈጥሮን በማሰናኘት የኢሬቻን ሌላኛው ገጽ ለማሳየት እጅግ ምቹ ነው።

ኢሬቻ ሰላምና መቻቻልን ዓብይ ትኩረቱ በማድረግ በአደባባይ የሚከበር በዓል ነው፡፡ በዓሉ፤ ከማህበራዊ፣ ሃይማኖታዊና ኪነ ጥበባዊ ፋይዳው ባለፈ፤ የቱሪስት መስህብ በመሆን ኢኮኖሚው ላይ የራሱን ሚና መጫወት እንደሚችል ሙያተኞች ይናገራሉ። ከዚህ አንጻር የኢሬቻን መልከ ብዙ ፋይዳዎች በኪነ ጥበባዊ ሥራዎችና በሌሎች ዘዴዎችም አጉልቶ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡

በአብርሃም ገብሬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review