የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ
ኢትዮጵያ በትውልድ ቅብብሎሽ እየተገነባች የመጣች ሀገር ናት፡፡ ሀገሪቱን አሁን ካለችበት ደረጃ ለማድረስ በየዘመኑ የነበረው ትውልድ የራሱን አሻራ አሳርፎአል፡፡ ሆኖም የሀገር ግንባታ ሂደት በመሆኑና በአንድ ትውልድ ብቻ ተሰርቶ ስለማያልቅ ቀጣይነት ያለው ስራ መስራት አስፈላጊ መሆኑን ምሁራን ይስማሙበታል፡፡
የትውልድ ድምር ውጤት በሆነችው ኢትዮጵያ፤ የዛሬው ትውልድ የትላንት ወራሽና ባለአደራ ብቻ መሆን የለበትም። የተሻለ ዛሬና ነገን የመፍጠር ኃላፊነት አለበት፡፡ ስለዚህ ያለፈውን ታሪክ ከመዘከር ባለፈ ለተተኪው የተሻለች ሀገር ለማስተላለፍ በሁለንተናዊ መልኩ መስራት ይጠበቅበታል፡፡
በጥበብ እድገት ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተወካይ ምክትል ርዕሰ መምህር እሱእንዳለ በቀለ ለዝግጅት ክፍላችን በሰጡት አስተያየት፣ ኢትዮጵያ በቀድሞ ታሪኮቿ የምትዘከር ብቻ መሆን የለባትም፡፡ የድል አድራጊነት ጉዞዋን በተለያዩ አግባቦች ማስቀጠል ያስፈልጋል፡፡ የዛሬ አስራ አራት ዓመት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን አንድ ብለን መሰረት ስንጥል የይቻላል መንፈስን በማንገብ በሀሳብ፣ በጉልበትና በገንዘብ ድጋፍ አድርገናል፡፡ በውጤቱም ዳግም ዓድዋን የማጣጣም እድሉን አግኝተናል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
“ግድቡ የኔም ነው” በሚል ስሜት በርካታ ልጆች ወላጆቻቸው ከሚሰጧቸው ገንዘብ ቆጥበው ቦንድ ገዝተዋል፡፡ ይህ አይነቱ ሀገራዊ ስሜት በቀጣይ የጋራ ጉዳዮቻችን ላይም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አክለዋል።
የስልክ መሸጫ ሱቅ ከፍቶ እየሰራ የሚገኘው ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት ሃይሉ ደቻሳ በበኩሉ፣ “ሀገራችን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የጀመረችው የልማት ስራ እጅግ የሚያበረታታ፤ ‘እንዲህም ይቻላል እንዴ’ የሚል ስሜት የጫረ ነው፡፡ ሰርቶ የሚያሰራ መሪ ካለን እኛም የሱን አሻራ የመከተል ሃላፊነት አለብን፡፡ ትውልድም ጥሩ አርዓያ የሚሆነው ካገኘ በተከፈተው በር ለመቀጠል የሚቸግረው ነገር አይኖርም የሚል እምነት አለኝ” ሲል ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ማጠናቀቅ መቻሉን በማሳያነት በማንሳት ተናግሯል።
የአሁኑ ትውልድ ያለፈውን ታሪክ ከመዘከር ባለፈ አሁን ላይ ምን እየሰራ ነው? በቀጣይስ ምን ይጠበቅበታል? በሚሉ ነጥቦች ዙሪያ የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ ለዝግጅት ክፍላችን ሀሳባቸውን አጋርተውናል፡፡ በማብራሪያቸው፣ “በታሪክ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያውያን በመተባበራቸው ያስመዘገቧቸው የተለያዩ ድሎች አሏቸው፡፡ በተደጋጋሚ የተቃጣባቸውን የውጪ ወረራ ‘አሻፈረኝ’ በማለት ለመላው ጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌት መሆን ችለዋል፡፡ በዚህም በህዝቦች መተባበርና መደጋገፍ ለሀገራቸው ነጻነት የተዋደቁባቸውን ድንቅና አኩሪ ድሎች በታሪክ መዝገብ ጽፈዋል፡፡ ህዝቦቿ የቱንም ያህል የፖለቲካ ልዩነት ቢኖራቸውም የጋራ በሚሏቸው እሴቶቻቸው ላይ ፅኑ አቋም አሏቸው፡፡
የጋራ ትርክቶቻችን ከሆኑት መካከል የዓድዋ ድል አንዱ ነው፡፡ በዚህ የሀገርን ሉዓላዊነትና ነፃነት የመጠበቅ ሃላፊነት ውስጥ ሁሉም የየድርሻውን በመወጣት ድል ማስመዝገብ ተችሏል። ያለፉ ታሪኮቻችንን መዘከር ከፊታችን ለሚጠብቁን ትላልቅ ሀገራዊ ጉዳዮች ብርታት ይሆነናል፡፡
የአሁኑ ትውልድ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት አንስቶ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎች ለህዳሴ ግድብ የአቅማቸውን ድጋፍ ማድረግ ችለዋል፡፡ የሀገርን ሰላም ለማስጠበቅ ብሎም እርስ በእርስ ያለንን ግንኙነት የተሻለ በማድረግ በንግግር የሚያምን ማህበረሰብ የመፍጠር ትልም እውን እንዲሆን ሀገራዊ ምክክር መድረክ ተጠቃሽ ነው፡፡ ሂደቱን የሚያስተባብረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በተለያዩ ክልሎች በማቅናት ሃሳቦችን ብሎም ቅሬታ የፈጠሩ ጉዳዮችን አጀንዳ አሰባስቧል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ወጣቱ ቀጥተኛ ተሳታፊ በመሆን ሀገር ለወጠነቻቸው ትላልቅ አጀንዳዎች መፈፀም ቀኝ እጅ መሆን ይጠበቅበታል” ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ምረቃ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ “ታሪክ ሰምተናል፤ ታሪክ አይተናል፤ ታሪክ ተምረናል፤ ዛሬ ፈጣሪ የመረጠው ትውልድ መሆን ስለቻልን ታሪክ ሰርተን፤ ታሪክ ላይ ቆመን ለማውራት በቅተናል” ብለዋል፡፡ የትላንትናውን ታሪክ በመናገር ጊዜ አናባክንም፤ የህዳሴን ፋይል በመዝጋት በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ሌሎች በርካታ ስራዎች ለመከወን እንዳቀዱም ጠቁመዋል፡፡
የህዳሴ ግድብን የሚስተካከል ለሠላማዊ ዓላማ የሚውል የኑክሌር ማብላያ ስራ እንደሚጀመር የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአፍሪካ ግዙፍ የአየር መንገድ ግንባታ ስራም እንደሚከናወን ገልፀዋል፡፡ በጥቂት ሳምንታት የነዳጅ ፋብሪካ ምረቃ በማካሄድ፤ በዕለቱ አስር እጥፍ የሚሆነው 2ኛው የጋዝ ፋብሪካ ግንባታን በማስጀመር የነዳጅ ባለቤት የመሆን የዘመናት ህልማችን እውን የሚሆንበት የነዳጅ ማጣሪያ ስራ እንደሚጀምር መግለፃቸው ይታወሳል፡፡
እንዲሁም የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ስራ፤ በቀጣይ አምስት ዓመት 1 ነጥብ 5 ሚሊየን ቤቶች ግንባታ፤ በድምሩ ከ30 ቢሊየን በላይ ዶላር ወጪ የሚጠይቁ፣ አፍሪካውያንን ቀና የሚያደርጉ እና የኢትዮጵያን ብልፅግና የሚያበስሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች እንደሚሰሩ ገልፀዋል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር አህመድም፤ “በተገፋን መጠን የማንገፋ፣ በተጫነብን መጠን የማንሸነፍ አይነት ሰው መሆን ያስፈልጋል። ክብራችንን አሳልፈን የማንሰጥ ሰዎች መሆን አለብን። የትውልድ ቅብብሎሽን እውን ለማድረግ ሲታሰብ ኃላፊነቱ የብዙሃኑ ነው፡፡ ትውልድን የመገንባት ኃላፊነት ለአንድ አካል ብቻ የሚተው አይደለም። ጉዳዩ ለመንግስት፣ ለመምህራን፣ ለሐይማኖት ተቋማት አልያም ለወላጅ ብቻ የሚተው ኃላፊነት አይደለም፡፡ ሁሉም የሚሳተፍበት እና ፍሬውን አብሮ የሚያጣጥምበት መሆን ይገባል” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የትውልድ ግንባታ ከቤተሰብ ይጀምራል፡፡ አንድ ህፃን ወላጆቹ የሚያደርጉትን አተኩሮ ይመለከታል። ለምሳሌ ያክል ወላጆቹ አንባቢ ከሆኑ እሱም ለማንበብ ጥሩ ፍላጎት ይኖረዋል። በሌላ በኩል ቤተሰቦቹ ሱሰኛ ከሆኑ እርሱም ያንኑ ለማድረግ ይሻል፡፡ ከዚህ አኳያ ቤተሰብ ልጆቹ በስነ ምግባር የታነፁ፣ ጠንካራ ሰራተኛና ሀገራቸውን የሚወዱ እንዲሆኑ ግዴለሽነት ሳያሳይ በትዕግስት መስራት እንደሚጠበቅበት ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ያነሳሉ፡፡
ትውልዱ የተሻለ ታሪክ ሰሪ እንዲሆን በማንነቱ የሚተማመንና የሚኮራ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህም በራስ አቅም ለሚሰሩ ስራዎች ዋጋ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ሀገር በቀል እውቀቶችን ጥቅም ላይ በማዋል ሁሉንም ጉዳይ ባለቤት እንዲኖረው ማስቻል ያስፈልጋል፡፡ በእድሜ የገፉ አባቶች ለታዳጊዎች የህይወት ተሞክሯቸውን የሚያስረዱበት አግባብ እንዲኖር ማመቻቸት እንዲሁም ደግሞ በስራ የሚያምን ትውልድ እንዲኖር የፈጠራ ስራዎችን ከማበረታታት ባሻገር ስራ ጠባቂ ትውልድ እንዳይኖር መንገዶች ቢመቻቹ መልካም እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡
ከአሁኑ ትውልድ ሀገራችን በርካታ ነገር ትጠብቃለች የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ፤ ድህነትን የሚጠየፍ ትውልድ በሚማረው ትምህርትና በሚሰራው ስራ ውጤታማ ለመሆን ፅኑ አቋም ሊኖረው ይገባል፡፡ የመመረቂያ ጥናታዊ ፅሁፎች መደርደሪያ ከማሞቅ በዘለቀ በትክክል መሬት ላይ ወርደው ጥቅም እንዲሰጡ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
እንደ ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ገለፃ፤ ትውልዱ ዘመኑ ከሚያስገኛቸው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግኝቶች ጋር በመናበብ ዓለም የደረሰባቸውን የፈጠራ ስራዎች ወደራስ በማምጣት ለማህበረሰቡ ችግር ፈቺ ተግባራትን መከወን ይጠበቅበታል፡፡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ግኝቶች ለበርካታ ዜጎች እፎይታን የፈጠሩ ናቸው፡፡ ጊዜን፣ ጉልበትን እንዲሁም የሀብት ብክነትን የሚቀንሱ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተደራሽ በተደረጉ ልክ ወደ ሌሎች የልማት አጀንዳዎች ትኩረት ለማድረግ እድል ይፈጥራል፡፡
በተጨማሪም ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦችን በመሰንዘር እንዲሁም በቀጣይ የኮሚሽኑ አጀንዳ ላይ ንቁ ተሳትፎ የማድረግ ኃላፊነት ይኖርበታል፡፡ እንደ ሀገር ያስመዘገብናቸውን ድሎች ተከትሎ መንግስት በቀጣይ ለመስራት ያሰባቸውን ሜጋ ፕሮጀክቶች፣ የባህር በር የማግኘት ጉዳይን ትውልዱ በሁለንተናዊ መልኩ መደገፍ እንደሚገባው ሃሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
በሄለን ጥላሁን