ተመልካችን ወደሜዳ የመለሰው የ‘ህዳሴ ዋንጫ’

You are currently viewing ተመልካችን ወደሜዳ የመለሰው የ‘ህዳሴ ዋንጫ’

መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ከአደረጉ የእግር ኳስ ክለቦች በተጨማሪ በተጋባዥነት ከሚቀላቀሉ ቡድኖች መካከል የሚደረግ ውድድር ነው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ)። ለአስራ ስምንት ጊዜ በተከናወነው ውድድር የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ሰባት ጊዜ አሸናፊ በመሆን ቀዳሚነቱን ሲይዝ የኢትዮጰያ ቡና እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ እግር ኳስ ልለቦች ሶስት ሶስት ጊዜ የዋንጫው ባለድል ሆነዋል። የዳሽን ቢራ እና ባህር ዳር ከነማ እግር ኳስ ክለቦች ደግሞ ወደ መዲናዋ ውድድር በተጋባዥነት መጥተው ውድድሩን ያሸነፉ ክለቦች ስለመሆናቸው የሶከር ኢትዮጵያ መረጃ ያመላክታል።

ለ19ኛ ጊዜ እየተካሄደ የሚገኘው የዘንድሮው የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) ‘ህዳሴ ዋንጫ’ በሚል ስያሜ ከባለፈው እሁድ አንስቶ መካሄድ ጀምሯል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በየዓመቱ የሚያዘጋጀው ይህ ውድድር በስምንት ክለቦች መካከል እየተከናወነ ይገኛል። ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ መቻል፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ፋሲል ከነማ፣ አዳማ ከተማ እና ሸገር ከተማ ተሳታፊ የእግር ኳስ ክለቦች ናቸው። በምድብ ‘ሀ’ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ፋሲል ከነማ፣ አዳማ ከተማ እና መቻል፤ በምድብ ‘ለ’ ኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ፣ ሸገር ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሁለት ምድብ ተደልድለው ነው ውድድሩ የተጀመረው።

በአዲስ አበባ ስታዲየም እየተካሄደ የሚገኘው የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ዋንጫ ከውድድሩ ዓመት መግቢያ በፊት የሚካሄድ ቀላል የትዕይንት የፉክክር መድረክ ብቻ አይደለም። በተለይም ለዋና ከተማዋና ለአካባቢው ክለቦች፣ ለደጋፊዎች እና ለእግር ኳስ ማህበረሰቡ ትልቅ ፋይዳና አስፈላጊነት ከፍተኛ ነው። የአዲስ አበባ ሲቲ ካፕ ዋንጫ የመጀመሪያው እና ዋነኛው ጠቀሜታ ለአሰልጣኞችና ለክለቦች እንደ አቋም መለኪያ ያገለግላል። የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ዋና አሰልጣኝ ዐቢይ ካሳሁን እንደሚሉትም ውድድሩ እንደ አቋም መለኪያ ጨዋታ እንደሚጠቅማቸውና በክረምት የዝውውር ወቅት ወደ

ክለቦች የተቀላቀሉ አዳዲስ ተጫዋቾች በይፋዊ ጨዋታዎች ተፈትነው ብቃታቸው የሚመዘንበት ወሳኝ መድረክ ነው።

በውድድሩ ላይ እየተሳተፉ ያሉ ክለቦች አሰልጣኞች በሰጡት አስተያየት የተጫዋቾችን ከቡድኑ ጋር የመዋሃድ ፍጥነት፣ አቋምና ቁመና እንዲሁም በስልጠና ላይ ያሳዩትን ነገር ወደ ትክክለኛ የጨዋታ ሁኔታ የመቀየር ብቃት ለመመልከት ዕድል ይፈጥራል። የታክቲክ አደረጃጀቶች በፉክክር ውስጥ ሲሞከሩ፣ የቡድኑ ጥንካሬዎችና ድክመቶች በግልጽ ይታያሉ። ይህ ደግሞ አሰልጣኞች የዋናው ሊግ ከመጀመሩ በፊት ማስተካከያዎችን እንዲያደርጉና የሚፈልጉትን የመጨረሻ ተጫዋቾች ምርጫ ለመወሰን ይረዳቸዋል።

በተለይ ከታችኛው ሊግ ለተጨመሩ ወጣትና ተስፋ ለሚጣልባቸው ተጫዋቾች፣ በሲቲ ካፕ ላይ የሚታይ ልዩ ብቃት በቶሎ የብዙዎችን ቀልብ እንዲስቡ ይረዳል። በዋናው ሊግ ውስጥ ቦታ ለማግኘት የሚደረገውን ፉክክር ከፍ የሚያደርግ እና ተጫዋቾቹ ለራሳቸው ያላቸውን ግምት የሚያጎለብት ነውም ተብሎለታል የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ። እንደ አሰልጠኝ ዐቢይ ካሳሁን አስተያየት ከሆነም ሲቲ ካፑ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ የሚጫወተው ሚና ከመደበኛ የወዳጅነት ውድድር እጅግ የላቀ ነው። የቡድን ዝግጅት ማሟሻ፣ የደጋፊ ስሜት መለኪያ እና ለታክቲክ ለውጦች መሞከሪያ ሆኖ ያገለግላል።

የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ መጀመር ይዞት የመጣው ሌላኛው ዜና ውድድሩ በተናፋቂው አዲስ አበባ ስቴዲየም መካሄዱ ነው፡፡ ለዓመታት በዕድሳት ላይ የቆየው የአዲስ አበባ ስታዲየም ለኢትዮጵያ ዋንጫ ፍጻሜ በሩን ከፍቶ የእግር ኳስ ተመልካቾችን አስተናግዷል። ሲቲ ካፑን እንደ ተሞክሮ በማየት የፕሪሚየር ሊግ ሼር ካምፓኒው የሚያዘጋጀው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድርም ወደ ቤቱ እንዲመለስ መንገድ ጠራጊ ስለመሆኑም የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ያስረዳል፡፡

በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ያሉ የከተማዋ ተቀናቃኝ ክለቦች ሲገናኙ ትልቅ የደጋፊን ስሜት ያነቃቃልና እግር ኳሱ ከዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም መመለሱ በስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ የፈጠረው የደስታ ስሜት ቀላል አይደለም። በእርግጥም የአዲስ አበባ ስታዲየም ከኮንክሪትና ብረት የተገነባ ሕንጻ ብቻ ሳይሆን፣ የሀገሪቱ የስፖርት ህያው ታሪክ፣ ለዓመታት የፍቅር፣ የፉክክርና የጋለ ስሜት መገለጫ ሆኖ ቆይቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዳዊት ትርፉ ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም እንዲመለሱ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል። የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከብዙ ዓመታት በኋላ በአዲስ አበባ ስታዲየም ተመልካቾች ገብቶ እንዲመለከትና የሚወዱትን ክለብ እንዲደግፉ ለማድረግ እና ከስታድየም በሚገኝ ገቢ የፋይናንስ አቅማቸው እንዲያጠናክሩ ለማድረግ ብዙ ርቀት መሄዱ ይታወቃል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅን ተከትሎ የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ (ሲቲ ካፕ) ‘ህዳሴ ዋንጫ’ የሚል ስያሜ የተሰጠው ሲሆን በደመቀ ሁኔታ በተመልካቾች ታጅቦ ውድድሩ እየተካሄደ ይገኛል። የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንደገለፀው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር የዲጂታል ቲኬቲንግ ስርዓትን በመጠቀም እንደ ከዚህ ቀደሙ ተመልካቾች ረጃጅም ሰልፎች ተሰልፈው ቲኬት የሚቆርጡበት ስርዓት እንዲቀየርም እየተከናወነ ይገኛል፡፡

19ኛው አዲስ አበባ ከተማ ‘ህዳሴ ዋንጫ’ በአዲስ አበባ ስታዲየም ሲጀመር የመቻል እግር ኳስ ክለብ የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ አሸንፏል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን ጨምሮ ተጋባዥ የክብር እንግዶች ያስጀመሩትን ጨዋታ መቻል 4ለ0 አሸንፏል። ካለን ኮፊ እና ዮሴፍ ታረቀኝ የመቻል ግቦች ባለቤት ሆነዋል። መቻል ተጨማሪ ግብ የሚያገኝበትን እድል ሞሃመድ አበራ ፍፁም ቅጣት ምት አምክኗል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ግብ ጠባቂው ብክ ኩሄዝ በሁለት ቢጫ ቀይ ካርድ ተመልክቶ ከሜዳ ሲወጣ የመቻሉ ቸርነት ጉግሳ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ በመመረጡ የ20 ሺህ ብር እና የክሪስታል ዋንጫ ሽልማት ተበርክቶለታል።

የአዲስ አበባ ከተማ ‘ህዳሴ ዋንጫ’ ቀጥሎ ሲካሄድ ኢትዮጵያ ቡና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን 3ለ1 አሸንፏል። ለኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ ሱራፌል ሹም በዛ እና አማኑኤል አድማሱ በጨዋታ ዲቫይን ዋቹኩዋ በፍፁም ቅጣት ምት ሶስቱን ግቦች ከመረብ አሳርፈዋል። አዲስ ግደይ የንግድ ባንክን ብቸኛ ግብ ሲያስቆጥር የኢትዮጵያ ቡናው ዲቫይን ዋቹኩዋ የጨዋታው ኮከብ ተብሎ በመመረጡ የ20 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶለታል።

ከትላንት በስተያ በተከናወነው እና  አምስት ግቦች በተቆጠሩበት ጨዋታ የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ፋሲል ከነማን ያሸነፈ ሲሆን፣ በቀጣይ ቀናትም ውድድሮች እንደሚቀጥሉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ መረጃ ያሳያል፡፡

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review