በምክክር ሰላምን ለማረጋገጥ ሴቶችን፣ ወጣቶችን እና አካል ጉዳተኞችን በንቃት ማሳተፍ ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አረዓያ (ፕ/ር) ገለጹ።
ኮሚሽኑ ‘የሴቶች፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች ሚና ለሀገራዊ ምክክር ስኬታማነት’ በሚል መሪ ሀሳብ በሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ሐረሪ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ አስተዳደር የውይይት መድረኮች እያካሄደ ይገኛል።
ውይይቱን አስመልክቶም የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አረዓያ (ፕ/ር)፣ በምክክር ሰላምን ለማረጋገጥ ሴቶችን፣ ወጣቶችን እና አካል ጉዳተኞችን በንቃት ማሳተፍ ይገባል ብለዋል።
ኮሚሽኑ አጀንዳ ባሰባሰበባቸው የምክክር ምዕራፎች ሴቶች፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች በንቃት መሳተፋቸውን አስታውሰው፣ እነዚህ ባለድርሻዎች ሀገራዊ ሰላምን ለማረጋገጥ የማይተካ ሚና እንዳላቸው ጠቁመዋል።
ሀገራዊ የምክክር ሂደቱ የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣም ባለድርሻዎቹ ትልቅ ኃላፊነት እንዳላበቸው የገለጹ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ መድረኮችን በመፍጠር ከሴቶች፣ ወጣቶች እና አካል ጉዳተኞች ጋር ግንኙነቱን በማጠናከር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።