የሆረ አርሰዴ ኢሬቻ በዓልን ለማክበር አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ እንግዶችን የተቀበሉ መሆናቸውን የቢሾፍቱ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አለማየሁ አሠፋ ገለጹ።
የቢሾፍቱ ከተማ ዘንድሮ በኮሪደር ልማት ተውባ እንግዶቿን በደማቅ ሁኔታ መቀበሏንም ጠቅሰዋል።
የሕዝብ በዓል የሆነው የኢሬቻ በዓል የምስጋና ፤ የወንድማማችነት፣ የአብሮነት እና የአንድነት በዓል ነው።
ከንቲባው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ታቅደው ተግባራዊ እየተደረጉ ባሉበት ጊዜ መከበሩ ልዩ ያደርገዋልም ብለዋል።
ኢሬቻ የገዳ ስርዓት መገለጫ ነው ያሉት ከንቲባው አብሮነት፣ወንድማማችነት እና አንድነት የሚንጸባረቅበት በዓል መሆኑንም ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ለበዓሉ መከናወን ያለባቸውን የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በማጠናቀቅ እንግዶችን በኢትዮጵያዊነት የእንግዳ አቀባበል ስርዓት መቀበሉንም ገልጸዋል።
ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ተስማሚ እና ለበዓሉ ተሣታፊዎችም የተመቸች በማድረግ ረገድ በርካታ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።

ከተማዋን ከዚህም በላይ የተሻለች እና ግንባር ቀደም የቱሪዝም መዳረሻነቷን ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።
በበዓሉ የሚታደሙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ምንም ዓይነት የአቅርቦት ችግር እንዳይገጥማቸው ከተለያዩ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በጋራ በመሆን ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ በከተማዋ ዋና ዋና ጎዳናዎችና በዓሉ በሚከበርበት ሥፍራ በዘመናዊ የደኅንነት ካሜራዎች የታገዘ የጸጥታ ሥራ እንደሚጠናከርም ገልፀዋል።
ነዋሪዎች በጋራ ሆነው እንግዶችን እየተቀበሉ ይገኛሉ ያሉት ከንቲባው ወደ ቢሾፍቱ ለመጡ እንግዶች መልካም አቀባበል ላደረጉ የከተማዋ ነዋሪዎች ምስጋናም አቅርበዋል።
እስከ በዓሉ ፍጻሜም ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ማሳሰባቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።
የዘንድሮው ኢሬቻ ” ኢሬቻ ለሀገር ማንሰራራት ” በሚል መሪ ቃል እየተከበረ ነው።