ቻይና በነፋስ የሚሞላ የዓለማችን ትልቁን ተንሳፋፊ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ተርባይን የተሳካ ሙከራ አደረገች፡፡
የንፋስ ተርባይኖች ቻይና ታዳሽ ኃይል ለማምረት በምታደርገው ጥረት ትልቅ ሚና ይጫወታሉ፡፡
ነገርግን ሀገሪቱ ወጪን ለመቀነስ እና የኃይል አቅርቦት አቅምን ለማሻሻል የሚረዱ መንገዶች ፍለጋዋን እንደቀጠለች ነው።
ይህም ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት በተፈለገበት ቦታ በቀላሉ መንቀሳቀስ የሚችል በነፋስ የሚሞላ ተርባይን እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።
የኤስ 1500 ተንሳፋፊ የንፋስ ኃይል ሥርዓት፣ ባለ 13 ፎቅ ህንፃ ቁመት እና የቅርጫት ኳስ ሜዳ ያህል ስፋት ያለው መሆኑ ተገልጿል።
በቤጂንግ ሊንዪ ዩንቹዋን የኃይል ቴክኖሎጂ የለማው ግዙፉ ተንሳፋፊ የነፋስ ኃይል ማመንጫ ተርባይን፣ የአውሮፕላን ሞተር የሚመስል ቅርፅ ያለው ሲሆን፣ እስከ 1 ሺህ 500 ሜትር ከፍታ ድረስ ሊሠራ እንደሚችል ተነግሯል፡፡
በዚህ ከፍታ ላይ ነፋሳት ከተለመዱት 200 ሜትር ከፍታ ካላቸው ማማዎች የተሻለ ፍጥነት እና ወጥነት ያላቸው ሲሆን፣ የሚፈለገውን ኃይል ለማመንጨት እንደሚያስችሉም ተጠቁሟል፡፡
በሙከራ ወቅትም አንድ ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ በማምረት በዓይነቱ የመጀመሪያው መሳሪያ ሆኖ በታሪክ መመዝገቡን የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ ያመለክታል፡፡
በታምራት ቢሻው