የኢሬቻ በዓል ባህላዊ ትውፊቱን ጠብቆ መከበሩ ሃገራዊ ማንሰራራትን ከማረጋገጥ ረገድ ትልቅ ድርሻ እንዳለዉ የበዓሉ ታዳሚዎች ተናግረዋል።
የሆረ ሀርሰዴ የኢሬቻ በዓል በመልካ ሆረ ሀርሰዴ ‘ኢሬፈና’ ምስጋና የማቅረብ ሥነ-ሥርዓት በማከናወን ተከበሯል።
በበዓል ላይ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል። ወጣት ሸገር ለገሠ በዓሉን ለመታደም ሆረ አርሰዴ የተገኘ ሲሆን፣ ድንቅ የሆነው የኢሬቻ በዓል ባህላዊ ትውፊቱን ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ሊተላለፍ እንደሚገባ ገልጿል።
የበዓሉ አከባበር ደማቅ እና ህብረብሔራዊ አንድነት የተፀባረቀበት መሆኑን ወጣቱ ገለፆ፤ በዓሉ አካታች በሆነ መለኩ መከበሩ ለሀገራችን አንድነትና ብልጽግና መረጋገጥ የራሱን ድርሻ ያበረክታል ብሏል።

ሌላው ታዳሚ አቶ ዳንኤል ተፈራ በሆረ ሀርሰዴ ኢሬቻ በዓል ማክበሪያ ስፍራው አካባቢ የተሰራው የማስዋብ ሥራና የተለያዩ አገልግሎት መስጫዎች መሟላታቸው ለበዓሉ ድምቀት፤ ለታዳሚዎች ደግሞ ምቾት ፈጥሯል ሲሉ ገልፀዋል።
በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ትልቅ ሥፍራ የሚሰጠው ኢሬቻ በዓል ሁል ጊዜ ባህሉን እና እሴቱን ጠብቆ በየአመቱ መከበሩ አብሮነትና ብዝሀነት እንዲጎለብት ከፍተኛ እገዛ አድርጓልም ብለዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የአሪ ብሔረሰብ አባል የሆኑት አቶ ማንአህለው ጥላሁን በበኩላቸዉ የአንድነት፣ የእርቅና የመከባበር መገለጫ የሆነው ኢሬቻ ከኦሮም ህዝብ አልፎ የብሄር ብሄረሰቦች የጋራ እሴት እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
አቶ ማንአህለው በዓሉን በወንድማማችነትና በአብሮነት በድምቀት እንዳከበሩም ተናግረዋል።
በበረከት ጌታቸዉ