የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ያለውን የኃይል አቅርቦት ለማሻሻል እየሰራ መሆኑን አስታቋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ዙሪያ የተገነቡ እና ጊዜያዊ የባለ ሶስት ፌዝ የጋራ ቆጣሪ ተጠቃሚ ለነበሩ 12 ሺህ 879 አባዎራዎች የነጠላ ፌዝ ቆጣሪ ቅየራ ማከናወኑን አገልግሎቱ ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ ገልጿል፡፡
የቆጣሪ ቅየራው የተከናወነው በኮየ ፈጨ 2፣ ፕሮጀክት 11፣12፣16፣17 እና 18 የ 20/80 እና በቦሌ በሻሌ ለሚገኙ 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለሆኑ 756 ብሎኮች መሆኑንም አመልክቷል፡፡
በተጠቀሱት ሳይቶች ላይ የቦሌ በሻሌ 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በስራ ሂደት ላይ ያሉ 900 ቀሪ ቆጣሪዎች ገጠማ በቀጣይ የሚከናዎን ሲሆን፣ የሌሎቹ ሳይቶች የቆጣሪ ቅየራ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁንም ነው ያመለከተው፡፡
የቆጣሪ ቅየራው የተከናወነው ቀደም ሲል የግል ቆጣሪ ለመግጠም የሚያስችል መሰረተ ልማት ያልተሟላ በመሆኑ ጊዜያዊ የኤሌክትሪክ ኃይል ሲጠቀሙ ለነበሩ ደንበኞች ሲሆን፣ አሁን ላይ መሰረተ ልማቱን ለመዘርጋት የሚያስችል ክፍያ ሙሉ በሙሉ በመከፈሉ ቆጠሪዎቹን መቀየር ተችሏልም ብሏል፡፡
በቆጣሪ ቅየራው ተቋማችን የ 19 ነጥብ 75 ኪሎ ሜትር የመካከለኛ መስመር ዝርጋታ፣ 100 ኮምፓክት ትራንስፎርመሮች ገጠማ እንዲሁም 12 ሺህ 879 ቆጣሪዎች ገጠማ እንዳከናወነም ጠቁሟል፡፡
የቆጣሪ ገጠማ ከተከናወነላቸው ጠቅላላ ደንበኞች ውስጥ 320 የሚሆኑት ቆጣሪዎች ለልማት ተነሺዎች የተገጠመ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡
በቀጣይ በቦሌ ቡልቡላ 20/80 የጋራ መኖሪያ ቤቶች የሚገኙ ጊዜያዊ ቆጣሪዎችን ለመቀየር ዝግጅት የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ መንገዶች ባለስልጣን በኩል የሲቨል ሥራው ሲጠናቀቅ የቆጣሪ ገጠማ ስራው ይከናወናልም ብሏል፡፡