የነዳጅ አቅርቦት፣ሥርጭትና ግብይት ቁጥጥር ሥርዓቱ በቴክኖሎጂ መታገዙ ተጠናክሮ ይቀጥላል

You are currently viewing የነዳጅ አቅርቦት፣ሥርጭትና ግብይት ቁጥጥር ሥርዓቱ በቴክኖሎጂ መታገዙ ተጠናክሮ ይቀጥላል

AMN መስከረም 26/2018

የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን የነዳጅ አቅርቦት፣ ሥርጭትና ግብይት ቁጥጥር ሥርዓቱ ፈጣን፣አስተማማኝና ጥራት ያለው እንዲሆን በቴክኖሎጂ የታገዙ አሠራሮችን ማጠናከሩን አስታወቀ።

በአዲስ አበባ ከ2014 እንዲሁም በክልሎች ከ2015 ጀምሮ የነዳጅ ግብይት በዲጂታል የክፍያ ዘዴ እየተከናወነ መሆኑን የባለሥልጣኑ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ በቀለች ኩማ ገልጸዋል።

ይህ አሠራር የዲጂታል ፖሊሲን ከመተግበር ባለፈ፤ በነዳጅ ግብይት ወቅት የሚፈጸሙ ሕገወጥ ግብይቶችን ለማስቀረት ማለሙን ተናግረዋል።

ማደያዎች የተጫነላቸው ነዳጅ በዲጂታል ግብይት ስለመፈጸሙ በየሩብ ዓመቱ ኦዲት እንደሚደረግና ሽያጫቸው ከ50 በታች የሆኑት በአዋጁ መሰረት ተጠያቂ እንደሚሆኑ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል 20 የክፍያ አማራጮች ወደ ሥራ መግባታቸውን እና ተገልጋዩ የሚመቸውን እንዲጠቀም እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በነዳጅ ግብይት ሠንሰለት ያሉ ሂደቶች በለማው ብሔራዊ የነዳጅ አቅርቦት ሠንሰለት አሥተዳደር ሥርዓት ውስጥ እንዲያልፉ እየተደረገ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ይህ ሥርዓት፤የነዳጅ ትዕዛዝ ከማደያ-የኩባንያ ማረጋገጫ-የነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የጭነት ጥያቄ ከኩባንያ-ከነዳጅ አቅራቢያ ለጂቡቲ ጭነት ትዕዛዝ – ከጂቡቲ የተጫነ – ጉዞ ላይ ያለ – ደርሶ የተራገፈ የሚሉትን ሂደቶች እንደሚያሳያይ አብራርተዋል።

ባለድርሻ አካላት የነዳጅ ትዕዛዝ ጭነት የት እና በምን ደረጃ ላይ እንዳለ የሚከታተሉበት ሥርዓት መሆኑን ጠቁመው፤ በዚህም በየዕለቱ ወደ ኢትዮጵያ የገባ እና ለማደያ የደረሰ የነዳጅ መጠን ይታወቃል፤ክትትልም ይደረጋል ብለዋል።

በሌላ በኩል የነዳጅ ጫኝ ቦቴ ተሽከርካሪዎች የመቆጣጠሪያ ፍሊት ማኔጅመንት የተሰኘ ሥርዓት እየለማ መሆኑን እና በቅርቡም ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

አሁን ካሉት 5 ሺህ 400 ቦቴዎች 3 ሺህ 193ቱ ጂ.ፒ.ኤስ ተገጥሞላቸው ወደ ሥርዓቱ መግባታቸውን እና በቀጣይ ሁሉንም ወደ ሥርዓቱ ለማስገባት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሥርዓቱ ምልክት ስለሚሰጥ ሁሉም ቦቴዎች ወደ ሥርዓቱ ሲገቡ መድረስ ካለባቸው ጊዜ ያለ አግባብ የሚዘገዩትን ተሽከርካሪዎች ለመቆጣጠር፣ነዳጅ መቀናነስ(ቅሸባን) ለመከላከል እንዲሁም ነዳጅን ከመዳረሻ ለመቀየር የሚደረግ ሙከራን ለማስቀረት እንደሚያስችል ማስረዳታቸዉን ተዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review