6ኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን መክፈቻ ስነ- ስርዓት በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።
በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ የኢፌድሪ ኘሬዝዳንት ታዬ አፅቀ ስላሴ እንደተናገሩት፣ ኢትዮጵያ በ2017 በጀት ዓመት 8.8 በመቶ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገቧን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ በግብርና ዘርፍ 1.57 ቢሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን የገለፁት ኘሬዝዳንቱ፣ ከ2016 በጀት አመት ጋር ሲነፃፀር የ24.7 በመቶ ብልጫ እንዳለው አመላክተዋል።

በኢንዱስትሪ የማምረት አቅም በ2017 በጀት ዓመት ወደ 65 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልፀው፣ በ2016 በጀት ዓመት 59 በመቶ ብቻ እንደነበር አስታውሰዋል።
በ2017 በጀት አመት ኢትዮጵያ 38.87 ቶን የወርቅ ምርት መገኘቱን አስረድተው፣ ባለፈው አመት ከተገኘው የ3.9 ቶን የወርቅ ምርት በንፅፅር የተገኘውን የምርት ዕድገት ገልፀዋል ። የሲሚንቶ ምርት በ2016 ከነበረው የ7.5 ሚሊዮን ቶን ወደ 9.1 ሚሊዮን ቶን ከፍ ማለቱን ገልፀዋል፡፡
በመክፈቻ ስነ-ስርዓቱ ላይ ከተገኙት ተጋባዦች መካከል የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ተጠሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ታዋቂ ሰዎች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
በሔለን ተስፋዬ