የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በሁለቱ ምክር ቤቶች የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር፤ የ2018 በጀት አመት በታሪካችን ውስጥ በጉልህ የሚወሳ አዲስ ምዕራፍ ሊሆን እንደሚችል አልጠራጠርም ብለዋል፡፡
በ2018 በጀት አመት መባቻ ላይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የተመረቀበት፣ የኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ሀብት የብስራት ጅማሮ የሆነው የተፈጥሮ ጋዝ የወጣበት እና የተፈጥሮ ሀብታችንን ለመጠቀም የዕድገታችን መልሕቅ የሆኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የተጀመሩበት መሆኑንም ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡
መንግስት ለበርካታ አመታት ሲያጠናና ሲዘጋጅበት ቆይቶ ተግባራዊ ባደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና ቀደም ሲል በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማስተካከያ ማእቀፍ ተይዘው በተከታታይ አመታት ሲተገበሩ በቆዩ ፕሮግራሞች ኢኮኖሚው በማንሰራራት ላይ እንደሆነም ነው ፕሬዚዳንቱ የገለጹት፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዘመናት በማዕቀፍ ተግዳሮቶች ተፅዕኖ ስር ወድቆ በከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ ይገኝ እንደነበር ያነሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ከለውጡ በፊት የተሰሩ ኢኮኖሚያዊ ስራዎች በዘላቂ የፋይናንስ መሰረት ላይ ያልተዋቀሩ፣ ሀገርን ለከፍተኛ እዳ የዳረጉ እና የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶችን የፈጠሩ ነበሩም ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ አክለውም፣ መንግስት እነዚህን የኢኮኖሚ መዛባቶች የሚያርሙ እና ወደ ብልፅግና ጎዳና የሚያደርሱ ፈጣንና መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ አድርጓል ብለዋል፡፡
በአስማረ መኮንን