በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ የግብጽ ተደጋጋሚ መሰረተ ቢስ ውንጀላ የቀጣናውን ሰላምና ዕድገት ካለመፈለግ የመነጨ መሆኑ ተገለጸ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከ14 ዓመታት ብርቱ ጥረት በኋላ በራስ አቅምና የሀገር ጥሪት ግንባታው ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃቱ ይታወቃል።
በግድቡ የግንባታ ሂደት በተለይም የውጭ ጫና እና የሀገር ውስጥ ባንዳዎች ፈተና የገጠመ ቢሆንም በመንግስት ቁርጠኝነት፣ በህዝቡ ትብብርና ያልተቋረጠ ጥረት ለስኬት በቅቷል።
የሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያም ባለፈ ቀጣናዊ የልማት ትስስርን መሰረት በመድረግ የጋራ ተጠቃሚነት መርህን የተከተለ መሆኑም ይታወቃል።
ከግንባታው ጅማሮ አንሰቶ እስካሁንም ከዚህ በተቃራኒ በመቆም የግብፅ መሰረተ ቢስ ውንጀላ እና የማደናገሪያ ሃሳቦች ግን አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በታላቁ የኢትይጵያ ሕዳሴ ግድብ ጉዳይ የግብጽ ተደጋጋሚ መሰረተ ቢስ ውንጀላ የቀጣናውን ሰላምና ዕድገት ካለመፈለግ የመነጨ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ አባይ ወርቁ፤ ኢትዮጵያ ሀብቷን አልምታ እንዳትጠቀም ብሎም የዕድገት ጉዞዋ እንዲገታ የግብጽ የዘመናት አሉታዊ እንቅስቃሴ አሁን ላይ ያከተመ ጉዳይ ሆኗል ብለዋል።
በመሆኑም በግብጽ አሁን ድረስ የቀጠልው ተደጋጋሚ መሰረተ ቢስ ውንጀላ የቀጣናውን ሰላምና ዕድገት ካለመፈለግ የመነጨ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሰሞኑ በሱዳን የተከሰተውን ጎርፍ ተከትሎ ግብጽ ችግሩን ከሕዳሴ ግድብ ጋር ለማያያዝ የሄደችበት ርቀትም የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላት ሆና ለመቀጠሏ ጥሩ ማሳያ መሆኑን በማንሳት እውነታውን ዓለም ሊገነዘበው እንደሚገባ አስረድተዋል።
በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል ሃላፊና መምህር ካሡ ጡሚሶ፤ ግብፅ የዓባይን ውሃ ለብቻዋ ለመጠቀም ካላት ፍላጎት የተነሳ የኢትዮጵያን ስም የማጠልሸትና የሀሰት መረጃዎችን የማሰራጨት ጥረቷን ገፍታበታለች ብለዋል።
በቅርቡ በሱዳን የተከሰተው የጎርፍ አደጋ በሕዳሴ ግድብ ምክንያት ነው በማለት የሀሰት መረጃ ማሰራጨቷ የዚሁ ማሳያ ስለመሆኑም አስረድተዋል።
የግብፅ የቆየ አስተሳሰብና የዓባይ ውሃን በብቸኝነት ልጠቀም ባይነት ለ21ኛ መቶ ክፍለ ዘመን የማይመጥን በመሆኑ የአሁኑ ትውልድ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት አድርጎ የአስተሳሳብ ለውጥ እንዲመጣ ሊጥር ይገባል ብለዋል።