የሽንት ፊኛ ስራ በዋናነት ሽንት ከኩላሊት ከተመረተ በኋላ ተቀብሎ ሽንት በማጠራቀም እንዲወጣ ማድረግ ነው።
የሽንት ፊኛ ዕጢ ህመም የተለያዩ ምክንያቶች ሲኖሩት ከእነዚያ ውስጥ አንዱ ሲጋራ ማጨስ ነው ተብሎ እንደሚታመን የተለያዩ ጥናቶችን ዋቢ አድርገው ያስቀመጡት በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጠቅላላ ቀዶ ጥገና እና የዩሮሎጂ ሰብ ስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር አህመድ አበበ መሀመድ ናቸው።

የሽንት ፊኛ ዕጢ ህመም ከተጠቀሰው ምክንያት በተጨማሪ የተለያዩ የፋብሪካ ኬሚካሎች፣ኢንፌክሽኖች ለምሳሌ ቢልሃርዚያ የተባለው በሽታ የሽንት ፊኛ የሚያጠቃ ስለሆነ ይህም አንዱ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ጠቅሰዋል።
እስፔስቶስ የተሰኘ ኬሚካል የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች የሚሰሩ ዜጎች በሽንት ፊኛ ዕጢ ሊጠቁ እንደሚችሉ ነው ዶ/ር አህመድ አበበ ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ የጠቆሙት፡፡
የሽንት ፊኛ ዕጢ ህመም ምልክቶች፡-
የሽንት ፊኛ ዕጢ ህመም የተለያዩ ምልክቶች የሚያሳይ ሲሆን፣ ከምልክቶቹ መካከል ሽንት ላይ ደም መታየት አንዱ ነው ብለዋል።

ማንኛውም ሰው በህይወት ዘመኑ በአጋጣሚ ከዓመት እና ከሁለት ዓመት በፊት ሽንቱ ላይ ደም ሊያይ እንደሚችል ያስረዱት ዶ/ር አህመድ፣ ምልክቱ ከታየ መዘናጋት እንደማይገባ አስገንዝበዋል።
ሌላኛው የበሽታው ምልክት የሽንት መዝጋት እና ማቃጠል ምልክት ሊኖር እንደሚችልም ገልፀዋ
የሽንት የመዝጋት ምልክት፡- ሽንት መቆራረጥ፣ ሽንት ማስማጥ የሽንት ጉልበት መቀነስ የሽንት መዝጋት ምልክቶች ናቸው ።
ምክንያቱ ደግሞ የሽንት ፊኛ ዕጢ ሽንት በትክክል በመስመሩ አንዳይወጣ ስለሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የማቃጠል ምልክቱ ሌላኛው የህመሙ መገለጫ ሲሆን፣ እነዚህም ሽንት ቶሎ ቶሎ መሽናት ለሊት ብዙ ጊዜ መነሳት እና ማጣደፍ እንዳለው ያብራራሉ፡፡
እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ያለ ግለሰብ በቶሎ ወደ ጤና ተቋም መሄድ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የሽንት ቧንቧ ኢንፌክሽን አብሮ ተያይዞ ሊመጣ እንደሚችል ገልፀዋል።
በተለይ በምርመራ ወቅት በአልትራሳውንድ እብጠት የሚታይ ከሆነ ሲስቶስ ኮፒ እና ሲቲ ስካን ምርመራ ተደርጎ የዕጢው ደረጃ ምን ያህል እንደሆነ በመለየት ህክምናው እንደሚደረግ ተናግረዋል።
የሽንት ፊኛ ዕጢ ህመም በቶሎ ከታወቀ በሽንት ቱቦ ጠርጎ በሚያወጣ መሳሪያ ማከም እንደሚቻል እና ሌሎች የህክምና ዓይነቶች መኖሩን ነው የተናገሩት ።
መከላከያ መንገድ፡-
ሲጋራ ማጨስ በማቆም በሽታውን መከላከል እንደሚቻል ተናግረዋል።
ለተለያዩ ኬሚካሎች የመጋለጥ ሁኔታን መቀነስ እና የኢንፌክሽን ሁኔታዎች ካሉ በቶሎ መታከም እንደሚገባ ሞያዊ ምክራቸውን ለግሰዋል።
ማንኛውም ሰው የሽንት መደፈረስ እና ከላይ የተጠቀሱ ምልክቶችን ካስተዋለ በፍጥነት ወደ ጤና ተቋም መሄድ እንዳለበት የጠቅላላ ቀዶ ጥገና እና የዩሮሎጂ ሰብ ስፔሻሊስት ሀኪም ዶክተር አህመድ አበበ መሀመድ ተናግረዋል
በሔለን ተስፋዬ