ቬትናማዊው ጎልማሳ ለ34 አመታት ጥፍሩን ባለመቆረጥ አሁን ላይ ጥፍሩ በደረሰበት ርዝመት በአለም ድንቃድንቅ መዝገብ ላይ ሊመዘገብ ችሏል።
ሉ ኮንግ ሁውየን የተባለው ግለሰብ የሁለት እጆቹ ጥፍሮች 19 ጫማ ወይም 5.9 ሜትር እንደሚረዝሙ አስደናቂ ጉዳዮችን የሚመዘግበው ጊነስ ወርልድ ሬከርድ አረጋግጫለሁ ብሏል።
የአለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ የሉ ኮንግ የጥፍር እርዝማኔ ከአንድ በአማካኝ ቁመት ጋር ከሚገኝ ቀጪኔ ጋር እንደሚስተካከል በንጽጽር አቅርቧል።
መምህር የመሆን ህልም እንደነበረው የሚናገረው ግለሰቡ፤ ከዛሬ 34 አመታት በፊት ጥፍሩን ላለመቆረጥ ሲወስን አሁን በሚገኘበት ደረጃ ይደርሳል ብሎ እንዳልጠበቀ ገልጿል፡፡
እጁ ላይ እንደ ገመድ ተጥመልምሎ የሚገኘውን ጥፍር ቢቆረጥ የስነ ልቦና ስብራት ሊደርስበት እንደሚችል የተናገረ ሲሆን፤ ሳይቆረጥ ከቆየበት ጊዜ አንጻር ከሰውነት ክፍሎቹ በሙሉ ለጥርፍሩ ልዩ ፍቅር እንዳለው አብራርቷል።
የግለሰቡ ጥፍር አሁን ለሚገኝበት ደረጃ መድረስ ነገሮች ቀላል እንዳልነበሩ የአለም ድንቃ ድንቅ መዝገብ ባሰፈረው ጽሁፍ አመላክቷል።
መመገብ፣ መተኛት እና ልብስ መቀየር ከጥፍር እድገቱ ጋር ተያይዞ ቀላል ባይሆንም ሉ ኮንግ እነዚህን ሁሉ ተግባራት ለመለማመድ እና የጥፍሩን እድገት ለማስቀጠል በርካታ ጥረት ማድረጉ ነው የተገለጸው።
ከሁለት እጆቹ ላይ ካለው ጥፍር በአውራ ጣቱ ላይ የሚገኝው ጥፍር በእርዝመቱ ከሁሉም የሚበልጥ ሲሆን አጠቃላይ ርዝመቱም 127 ሴንቲ ሜትር ነው ተብሏል።
የግድግዳ ላይ ስዕሎችን በመሳል የሚተዳደረው ግለሰቡ በአሁኑ ወቅት በወንድ ዘርፍ ረጂም ጥፍር ባለቤት ሬከርድን የያዘ ሲሆን 12 ሜትር ጥፍር ያላት አሜሪካዊት የዋናው ክበረ ወሰን ባለቤት ናት።
በዳዊት በሪሁን