የአዲስ አበባ ውበት ከሚያጎሉ ትዕይንቶች መካከል የአደባባይ በዓላት ግንባር ቀደም ናቸው ።
በአዲስ አበባ በወርሃ መስከረም ከመሰቀል በዓል ቀጥሎ የመዲናዋን ውበት ካጎሉ በዓላት አንዱ በድምቀት የተከበረው የኢሬቻ ሆረ ፊንፊኔ በዓል ነው።

በዚሁ በዓል ላይ የአዲስ አበባ ውበት ስለመጎምራቱ በርካቶች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ከአሪ ብሔረሰብ ብርቅዬ አቀንቃኞች መካከል አንዱ የሆነው ታሪኩ ጋንኪስ፣ ወይም ዲሽታ ግና የአዲስ አበባ ውበት ከግዜ ወደ ጊዜ በመጉላቱ መደነቁን ተናግሯል።
የአዲስ አበባ በኮሪደር ልማት መዋብ ለኢትዮጰያውያን መሆኑን አንስቷል።

ልማት እና ሰላም ለህዝብ የሚጠቅም ነገር በመሆኑ ይህንን ተግባር ማስቀጠል እንደሚገባም ነው የተናገረው።
መዲናዋ በጥሩ ሁኔታ አምራ እና ተውባ ተመልክቻታለሁ ያለው ድምፃዊው፣ አዲስ ልብስ ለብሰን እንደሚያምርብን ሁሉ ከተማዋም ስትለማ እንዳማረባት ገልጿል
ልማቱ ለሌሎች ሀገራችን ይችህ ናት እንድንል እንድንኮራባት እንድንመካባት ያደርጋል ሲል ተናግሯል።
ኢሬቻን በሆረ ፊንፊኔ ለማክበር ከሲዳማ ክልል የመጡት አቶ አሰፋ ኪያ በበኩላቸዉ በአዲስ አበባ የተሰሩ መሰረተ ልማቶች ከዚህ በፊት ከነበረው ፍፁም ልዩነት እንዳለው ጠቅሰዋል።

በአጠቃላይ በኮሪደር ልማት የተሰሩ ስራዎች የአፍሪካ መዲና የዓለም የዲፕሎማቶች መቀመጫነቷን በተግባር ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
አዲስ አበባ እንደስሟ አብባ አይቻለሁ ያሉት የበዓሉ ተሳታፊ፣ ልማቱ ለበዓሉ ልዩ ድባብ እንደፈጠረም ጠቅሰዋል።
በተለይም በዓሉ የሚከበርበት መልካ ሆረ ፊንፊኔ በዚህ መልኩ መሰራቱም በዓሉን ልዩ ውበት አጎናፅፎታል በማለት አስረድተዋል።

አርቲስት አበበች አጀማ፣ በሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ለማክበር ከተገኙ ታዋቂ የአፋን ኦሮሞ የኪነ-ጥበብ ሰዎች መካከል አንዷ ናት።
በዓሉ ከተሰራው የመሰረተ ልማት ጋር ተዳምሮ ለከተማዋ ልዩ ውበት ያላበሰ ሲሆን፣ በዓሉን በአንድነት፣ በፍቅር እና በደስታ ማክበራቸውን ተናግራለች
የአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር ልማትን ስትመለከት ውጭ ሀገር እንደሚመስላት ገልፃ፣ ከተማዋ እንደ ስሟ አዲስ መሆኗ እንዳስደሰታት ተናግራለች

አዲስ አበባ ሌላ አዲስ ከተማ መስሏል መልካ ሆረ ፊንፊኔ ደግሞ ተጨማሪ ድምቀት ፈጥሯል ያሉት የኦሮሞ አባገዳዎች ሰብሳቢ አባ ገዳ ወርቅነህ ተሬቻ ናቸው።
የመጫ አባገዳ ወርቅነህ እንደተናገሩት ፣ በዓሉ የሚከበርበት ስፍራ መግቢያው እና መውጫው በአግባቡ የተስተካከለ እና ያማረ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከእንጦጦ ጀምሮ የወንዙ ዙሪያ ሁሉ አረንጓዴ መልበሱ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበትን አላብሷታል ብለዋል።
በሔለን ተስፋዬ