የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራርመዋል ።
የፊርማ ስነ-ስርዓቱን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው አከናውነዋል ።
በዚሁ ወቅት መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተማ አስተዳደሩ ለሚያከናውናቸው ሁሉን አቀፍ ልማቶች ተባባሪ መሆኑን ጠቁመው ለዚህም ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።

ከተማ አስተዳደሩ እና አየር መንገዱ በተለያዩ ጉዳዮች በጋራ እየሰሩ መሆኑን ያስታወሱት ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምገባ መርሃ ግብር የተከናወኑ ስራዎች ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የሚያስፈልጉ ድጋፎችን ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያከናወናቸው የልማት ስራዎች አስደናቂ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከተማዋ ዘመናዊ፣ምቹ እና ተወዳዳሪ እየሆነች እንደምትገኝም ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ስራ አስፈጻሚው አየር መንገዱ ኢትዮጵያን እንደ ሀገር አዲስ አበባን እንደ ከተማ የማስተዋወቅ ስራውን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በከተማዋ ውስጥ የተከናወኑ የልማት ስራዎች የማስተዋወቅ ስራውን ለማሳለጥ እንደሚረዳም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የማኔጅመንት አባላት በመዲናዋ ውስጥ የለሙ እና እየለሙ የሚገኙ የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ልማቶችን ጎብኝተዋል።
በ- ሀብታሙ ሙለታ