ኢለን መስክ ግማሽ ትሪሊየን ዶላር ሀብት በማካበት የመጀመሪያው ሰው ሆነ

You are currently viewing ኢለን መስክ ግማሽ ትሪሊየን ዶላር ሀብት በማካበት የመጀመሪያው ሰው ሆነ

AMN- መስከረም 27/2018 ዓ.ም

የአለማችን ቁጥር አንድ ባለሀብት ኢለን መስክ የግማሽ ትሪሊየን ዶላር (500 ቢሊየን ዶላር) ባለቤት በመሆን ቀዳሚው ሰው ሆኗል።

የቴስላ የኤሌክትሪክ መኪና የገበያ ድርሻ ማደግ እንዲሁም ሌሎች ኢለን በባለቤትነት የሚያስተዳድራቸው ንግዶች ገቢ መጨመር ለሀብቱ ማደግ ምክንያት ናቸው ተብሏል።

የፎርብስ የቢሊየነሮች ዝርዝር ማውጫ የኢለን መስክ አሁናዊ የተጣራ ሀብት 500.1 ቢሊየን ዶላር እንደሚደርስ አስቀምጧል።

በቅርብ ወራቶች ከቴስላ የመኪና አምራች ኩባንያ በተጨማሪ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ማበልጸጊያ ኩባንያው “ኤክስ ኤ አይ” እና የሮኬት አምራች ድርጅቱ “ስፔስ ኤክስ” ከፍተኛ ትርፍ ማጋበሳቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

ነገር ግን የኢለን መስክ ዋነኛ ሀብት የሚመነጨው በቴስላ ኩባንያ ካለው የ12 በመቶ ድርሻ እንደሆነም ዘገባው ጠቅሷል።

መስክ አሁን የሚገኝበት የሀብት ደረጃ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ከሚፎካከሩት ባለሀብቶች ከፍ ብሎ እንዲቀመጥ የሚያስችለው ነው ተብሏል።

በፎርብስ የቢሊነሮች ዝርዝር ማውጫ መሰረት የኦራክል ቴክኖሎጂ ኩባንያ በ350 ቢሊየን ዶላር መስክን እየተከተለ ይገኛል።

ኢለን መስክ በመጪዎቹ አመታት የቴስላ ኩባንያን የገበያ ዋጋ በ8 እጥፍ ለማሳደግ ፣ 12 ሚሊየን የቴስላ መኪኖችን ለመሸጥ እንዲሁም አንድ ሚሊየን ሮቦቶችን ለገበያ ለማቅረብ አቅዷል።

ሆኖም በኤሌክትሪክ መኪና ሸያጭ ገበያው ላይ የቻይናው “ቢዋይዲ” እየፈጠረው የሚገኘው ተጽዕኖ ትልቅ ፉክክር እንደሚሆንበት ይጠበቃል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review