ቅጥራን ማንፋክቸሪንግ ሜዲካል ኢኩፕመንትስ ትሬዲንግ የግል ድርጅት በሀገር ውስጥ ያመረታቸውን የህክምና ግብዓቶችን የማስተዋወቅና የማስመረቅ መርሃ ግብር አካሂዷል ።
ተቋሙ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የህክምና መድሃኒቶች እና የህክምና መሳሪያዎችን አስተዋውቋል።
በመርሃ ግብሩ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍሬህይወት አበበ ጥራት መሰረት ያደረገ ፍትሃዊ ተደራሽ የሆነ የጤና አገልግሎት ለመስጠት መንግስት በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

ይህም በሀገር ውስጥ የህክምና ግብዓቶችን ማምረት የጤና ዘርፍ ለይ የሚታዩ ተግዳሮቶች የሚቀርፍ ነው ብለዋል። መንግስት የጤናው ዘርፍ ለማሻሻል የሚሰሩ የግል ተቋማትን ይደግፋልም ነው ያሉት ፡፡
የቅጥራን ማኑፋክቸሪንግ ሜዲካል ኢኪዮፕመንት ትሬዲንግ ፒ ኤል ሲ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አታኩሬ አያሌው እንደገለጹት ድርጅቱ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን በስሩ ከሚያስተዳድራቸው የኢንቨስትመንት ማዕከላት ውስጥ አንዱ ወደሆነው ቂሊንጦ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የሚገኝ የህክምና መሳሪያዎችን አምራች ሲሆን አሁን ባለው የሙከራ ስራ ሂደት 6 አይነት አጣዳፊ የህክምና መርጃ መሳሪያዎችን በማምረት ላይ ይገኛል ብለዋል።

ድርጅቱ የሀገር ውስጥ የህክምና መሳሪያዎች ምርትን በማብዛት የውጭ ምንዛሪን በማስቀረት ረገድ ሰፊ ድርሻን እንደሚይዝና አሁን ወደ ምርት ከገባ ጀምሮ የጉበት የጨጓራ የኤች አይ ቪ መመርመሪያ ምርቶችን በማምረት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ድርጅቱ በቀን በሚሊየን የሚቆጠሩ የመመርመሪያ ኪቶችን እያመረተ እንደሚገኝ እና ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠ የተገለፀ ሲሆን ከሩሲያ ጋር በትብብር ለመስራት የሚያስችል ስምምነትም ተፈራርሟል፡፡
ትላንት በተከናወነው የሁለቱ ምክር ቤት የመክፈቻ ስነ-ስርአት ንግግር ያደረጉት ኘሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ መሠረታዊ የጤና አገልግሎቶችን ከመስጠት ባሻገር መድሃኒቶችንና የህክምና መሣሪያዎችን በሀገር ውስጥ በማምረት ከፍተኛ ውጤት ተገኝቷል ማለታቸው የሚታወስ ነው ፡፡
በመርሃ ግብሩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎችን ጨምሮ የሩሲያ ኤምባሲ ተወካዮች ተገኝተዋል።
በመሀመድኑር ዓሊ