በቺካጎ ማራቶን የማሸነፍ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል መገርቱ ዓለሙ ቀዳሚዋ አትሌት ናት፡፡
መገርቱ የ2024ቱን ለንደን ማራቶን አራተኛ ሆና ስታጠናቅቅ የገባችበት ሁለት ሰዓት 16 ደቂቃ 14 ሰከንድ የራሷ የግል ምርጥ ሰዓቷ ነው፡፡ ከቺካጎ ተወዳዳሪዎች ቀዳሚዋ ፈጣን ሰዓት ባለቤት ያደርጋታል፡፡
ሐዊ ፈይሳም ሌላዋ ግምት ያገኘች አትሌት ናት፡፡ ሱቱሜ አሰፋ ባሸነፈችበት የ2025 ቶኪዮ ማራቶን ሶስተኛ ደረጃን ስታገኝ የገባችበት ሁለት ሰዓት ከ17 ደቂቃ ከቺካጎ ተሳታፊዎች ሁለተኛዋ ፈጣን አትሌት ናት፡፡
የባለፈው ዓመቱ ዱባይ ማራቶንን ስታሸንፍ የገባችበት ሁለት ሰዓት ከ18 ደቂቃ ከ27 ሰከንድ የራሷ የምንጊዜውም ምርጥ ሰዓት የሆነላት በዳቱ ሂርጳም ግምት ካገኙት ውስጥ ናት፡፡
የ2025ቱን የለንደን ማራቶን በአራተኛነት ስታጠናቅቅ የገባችበት ሁለት ሰዓት ከ19 ደቂቃ ከ17 ሰከንድ የራሷ ምርጥ ሰዓት የሆነላት ሄቨን ኃይሉ ሌላኛዋ የምትጠበቅ አትሌት ሆናለች፡፡
ኬንያዊያኑ ኢሪን ቼፕታይና ሜሪ ንጉጊ የኢትዮጵያውያን ዋነኛ ተፎካካሪዎች እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡
በወንዶች በኢትዮጵያ በኩል ሁሰዲን ሞሀመድ ኢሳ ይጠበቃል፡፡ በ2024ቱ የቺካጎ ማራቶን የብር ሜዳሊያውን ሲያጠልቅ የገባበት ሁለት ሰዓት ከ04 ደቂቃ ከ39 ሰከንድ የአትሌቱ የምንጊዜውም ፈጣን ሰዓቱ ነው፡፡
የማሸነፍ ትልቅ ግምት ካገኙት ኬንያውያን መካከል ከተወዳዳሪዎች ፈጣን ሰዓት ባለቤት የሆነው ጆን ኮሪር ይጠበቃል፡፡
የ2024ቱን ቺካጎ ማራቶን ሲያሸንፍ የገባበት ሁለት ሰዓት ከ02 ደቂቃ ከ44 ሰከንድ የራሱ ምርጥ ሰዓቱ ነው፡፡ ቲሞቲ ኪፕላጋት፣ አሞስ ኪፕሩቶና ሳይብሪያን ኮቱት ከኬንያ ሌሎች ለድል የተገመቱ አትሌቶች ናቸው፡፡
ቤልጄማዊ በሺር አብዲ፣ ኡጋንዳዊ ጃኮፕ ኪፕሊሞ፣ አሜሪካዊ ጋለን ሩፕ ሌሎች ቺካጎ ላይ የሚጠበቁ ውጤታማ አትሌቶች መሆናቸውን ኤ ቢ ኤስ ኒውስ ዘግቧል፡፡
በታምራት አበራ