የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ሕገ-መንግስታዊና ሕጋዊ አሰራርን በተከተለ አግባብ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ምላሽ እንዲያገኙ እንደሚደረግ በፌዴሬሽን ምክር ቤት የማንነት፣ የአስተዳደር ወስንና የሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት በ6ኛ የፓርላማ ዘመን 5ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ 1ኛ መደበኛ ስብሰባ የማንነት፣ አስተዳደር፣ ወስንና ሰላም ግንባታ ቋሚ ኮሚቴ የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃጸም ሪፖርትን በማዳመጥ የ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ ተወያይቶ አጽድቋል።

የቋሚ ኮሚቴው ጸሐፊ አቶ ፍቅሬ አማን፥ በህዝቦች በሚቀርቡ የማንነት፣ አስተዳደር ወሰንና ሠላም ግንባታ ጉዳዮች ላይ የተከናወኑ ተግባራት ከዚህ ቀደም ከሚቀርቡት አንፃር ሲታይ እየቀነሱ ነው ብለዋል።
በ2018 ዓ.ም በጀት ዓመት ለሚቀርቡ የማንነት ይታወቅልኝና የህዝብ ውክልና አቤቱታዎች በጥናት ላይ የተመሰረተ ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የብሔር፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች የማንነት መገለጫ (አትላስ) ጥናትን ለማስጀመር ከባድርሻ አካላት ጋር የተጀመሩ የምክክር መድረኮችን በማስቀጠል ቀሪ ተግባራት በማጠናቀቅ ወደስራ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በአስተዳደር ወሰንና እራስን በራስ የማስተዳደር የሚነሱ ጥያቄዎች ሕገ-መንግስታዊና ሕጋዊ አሰራርን በተከተለ አግባብ ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ምላሽ እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።

በሁሉም ክልሎች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትንና የሰላም እሴት ግንባታ ስራዎችን የሚያጠናክሩ የምክክር መድረኮች በስፋት ለማካሄድ መታቀዱንም አስረድተዋል።
በምክር ቤቱ ቀርበው የነበሩና ወደክልሎች የተላኩ አቤቱታዎችን አፈፃፀም በመገምገም የድጋፍና ክትትል ስራዎችን በማከናወን ህዝቦች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ይደረጋል ማለታቸዉን ተዘግቧል፡፡