ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልእክት በከተማችን የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱን የጠበቀ እና ቀልጣፋ ለማድረግ የጀመርነውን ስራ አጠናክረን ቀጥለናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትራችን ጋር በመሆን የአዲስ አበባ ከተማን የመሶብ የአንድ መዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎትን ስናስጀምር ቅርንጫፎችን በፍጥነት ለማስፋት በገባነው ቃል መሰረት፣ ዛሬ 12 የከተማ አስተዳደር እንዲሁም 3 የፌደራል ተቋማትን በመያዝ 96 የከተማ አስተዳደር አገልግሎቶች የሚሰጠውን የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ቦሌ ቅርንጫፍን ስራ አስጀምረናል ብለዋል፡፡

የቦሌ ክፍለ ከተማ የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ስራ ያስጀመርነው ባለ 6 ወለል ህንፃ በ4 ወራት ገንብተን፣ አስፈላጊውን ቴክኖሎጂ እና ግብአት አሟልተን እንዲሁም የሰው ሀይል አሰልጥነን ነው።

ይህንን የአዲስ መሶብ የአንድ መአከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት በአጭር ጊዜ ግንባታው እንዲጠናቀቅ እና በአስፈላጊው ቴክኖሎጂ እንዲዘምን ለደገፉን አካላት በሙሉ፣ በተለይም የኢትዮዽያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና ለከተማችን አመራሮች በተገልጋዩ ህብረተሰብ ስም ከልብ አመሰግናለሁ። ተገልጋዩ ህብረተሰብም በማዕከላቱ በመገኘት አገልግሎቶቹን እንድትጠቀሙ ጥሪዬን አቀርባለሁ በማለት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡