የ2018 ዓ.ም የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች የሚያሰሩ እና ዓለም አቀፍ ሁኔታን ያገናዘቡ መሆናቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ

You are currently viewing የ2018 ዓ.ም የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች የሚያሰሩ እና ዓለም አቀፍ ሁኔታን ያገናዘቡ መሆናቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ

AMN – መስከረም 28/2018 ዓ.ም

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ለሁለቱ ምክር ቤቶች ያቀረቧቸው የ2018 በጀት ዓመት የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች የሚያሰሩና ዓለም አቀፍ ሁኔታን ያገናዘቡ አቅጣጫዎች መሆናቸውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ፡፡

ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ባነሷቸው የመንግስት የትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ ኤ ኤም ኤን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ጋር ቆይታ አድርጓል።

ፕሬዝዳንቱ ያነሷቸው ሃሳቦች እና አቅጣጫዎች የሚያሰሩ ዓለም አቀፍ ሁኔታን ያገናዘበ መሆናቸውን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት ብርሃኑ ሌንጂሶ (ዶ/ር) ተናግረዋል።

አክለውም በተለይ ሀገራችን በሚቀጥሉት ዓመታት የዜጎችን ክብር፣ ፍላጎት እና ተጠቃሚነት ማዕከል አድርገው የሚሰሩ ስራዎች መሆናቸውን ያመላከቱ አቅጣጫ መሆናቸውን ነው የገለፁት፡፡

ፕሬዝዳንቱ በዓባይ እና በቀይ ባህር ላይ ያለውን አላማ ግልጽ ማድረጋቸው እጅግ የሚያበረታታ መሆኑንም አመላክተዋል ።

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በበኩላቸው፣ ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ የተፋሰሱ ሀገሮች ህብረት እንዲፈጥሩ እና ለጋራ ልማት እንዲተበበሩ ያነሱት ሃሳብ ወቅቱን የዋጀ ነው ሲሉ ነው የገለፁት ፡፡

ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሃገራት ጋር አብሮ የማደግ እና የመበልፀግ አቋም ስታራምድ ነበር አሁንም ይህንን አጠናክራ ታስቀጥላለች ነው ያሉት፡፡

የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ ዓለም አቀፍ መብት እንዳላት እና ይህንንም ለማሳካት ሰላማዊ በሆነ መንገድ፣ በድርድር እና ሰጥቶ በመቀበል መርህ የተመሰረተ መሆኑን ነው ያነሱት።

ሌላኛው የሕዝብ ተወካዮች የምክር ቤት አባል ዶ/ር መኮንን ጎሌሳ በበኩላቸው፣ ስለ ልማት የምናደርጋቸውን ነገሮች ከቃላት ባለፈ በተግባር ማየት የጀመርንበት ጊዜ መሆኑን ገልጸው፣ ፕሬዝዳንቱ በበጀት ዓመቱ ለመፈፀም ያነሷቸው አቅጣጫዎች ይህንኑ የሚያጠናክሩ ናቸው ብለዋል ።

በኢኮኖሚያዊ በቱሪዝሙ እና በግብርናው ዘርፉ በርካታ ልማታዊ ተግባራት እየተሰሩ እንዳሉ ህዝቡ ይረዳል ያሉት ወ/ሮ ሙሉ ሉባባ ኢብራሒም፣ ሰባተኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍትሀዊ እና በህዝቡ ዘንድ ተአማኒነት ያለው እንዲሆን መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ መረዳታቸውን አመላክተዋል ።

የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ ተግባራዊ እንዲሆኑ በማስቻል ረገድ የቁጥጥርና ድጋፍ ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል ለተግባራዊነታቸውም የድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል ፡፡

በ-ፍሬህይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review