የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ የነባሩን የተሽከርካሪ መለያ ሰሌዳ በአዲስ ለመተካት የሚያስችል አዲስ የተሽከርካሪዎች የመለያ ቁጥር ሰሌዳ ዓይነቶችና ምልክቶችን ይፋ አድርጓል፡፡
የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ (ዶ/ር)፥ አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ በትራንስፖርት ዘርፉ ትልቁ እርምጃ መሆኑን ተናግረዋል።
በስራ ላይ ያለው ሰሌዳ ከዘርፉ እድገትና ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር አብሮ የማይሄድ በመሆኑ አዲስ የተሽከርካሪ ሰሌዳ ማስፈለጉን ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ለህገወጥነት የተጋለጠ እና ለቁጥጥር ስርዓትም አመቺ አለመሆኑን ጠቅሰው፥ አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ በቴክኖሎጂ በታገዘ አሰራር የሚመራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሰሌዳው ስለተሽከርካሪው ሙሉ መረጃ የሚሰጡና ተቆጣጣሪ አካላት በቴክኖሎጂ የሚለዩዋቸው ሚስጥራዊ መረጃዎችን ያካተተ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህም ማጭበርበርን ሙሉ በሙሉ የሚያስቀር መሆኑን በማንሳት፥ የተሽከርካሪ ባለቤቶች በሚወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምዝገባ ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በ2018 ዓ.ም አዲሱን የተሽከርካሪ ሰሌዳ ሙሉ በሙሉ ለመተካት እቅድ መያዙን መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር ዴኤታ በርኦ ሀሰን በበኩላቸው አዲሱ ሰሌዳ እያደገ የመጣውን የተሽከርካሪ ቁጥር ማስተናገድ የሚያስችል መሆኑን አመላክተዋል።
አገራዊ የተሽከርካሪ ቋትን ለማደራጀት የሚያስችልና የፖሊሲ መሳሪያ ጭምር ሆኖ የሚያገለግል መሆኑን ገልጸዋል።