በትናንትናው እለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ሰባተኛው የታማኝ ግብር ከፋዮች የእውቅና ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመርሃ ግብሩ ከግብር አከፋፈል ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ ችግሮችን እና ሌብነትን ለመቀነስ የሚያስችሉ የአሰራር ስርአት መበልፀጋቸውንና ሌሎች አሰራሮችም በመተግበር ላይ መሆናቸዉን ጠቁመዋል፡፡ በዚህም ግብርን የሚያጭበረብሩ ግለሰቦች ቁጥር መቀነስ እንደተቻለም ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህ በፊት በቆሻሻ የምትታወቀውን መዲናችንን በእናንተ ገንዘብ እየተሰራች መሆንዋን በኩራት ልገልጽላችሁ እወዳለሁ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ መንግስት ኢትዮጵያን ለመቀየር እና ለማበልፀግ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል፣ ይህ ሊሳካ እና እውን ሊሆን የሚችለው ታማኝ አሰሪዎች በሚፈጥሩት የስራ እድልና በሚከፍሉት ግብር መሆኑን እናምናለን ብለዋል፡፡
የግሉ ሴክተር ከትርፍ በላይ ማህበራዊ አላማን ያነገቡ ስራዎችን መስራት እንደሚጠበቅበት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግስትም በችግሮች የሚታጠር ሳይሆን ለሚያጋጥሙ ችግሮችና ተግዳሮቶች የመፍትሄ አቅጣጫዎችን እያስቀመጠ ወደ ብልፅግና ጉዞ ይሻገራል ብለዋል፡፡
“በማንኛውም ጩኸት አንደነግጥም፤ በክብርም አንታለልም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያ ለመበልፀግ በምታደርገው ጥረት ለሚገጥማት ማንኛውንም ፈተና የመፍትሄ አቅጣጫዎችን እያስቀመጥንና እየፈታን ወደ እድገት እንገሰግሳለን ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፣ ሀገራችንን ለማሳደግ መንግስት እና ህዝብ በትብብር፣ በህብረትና በመተጋገዝ ወደ ሚቀጥለው ደረጃ ለማሸጋገር በትጋት እንስራ ሲሉም አሳስበዋል፡፡
በአስማረ መኮንን