እስራኤል እና ሀማስ ትራምፕ ባቀረቡት የሰላም ስምምት ሀሳብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ ከስምምነት ደረሱ

You are currently viewing እስራኤል እና ሀማስ ትራምፕ ባቀረቡት የሰላም ስምምት ሀሳብ የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ ከስምምነት ደረሱ

AMN – መስከረም 29/2018

ለሁለት አመታት በጦርነት ላይ የሚገኙት እስራኤል እና ሀማስ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ መስማማታቸውን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስታውቀዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ባቀረቡት የሰላም ስምምነት ሀሳብ ዙሪያ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ በግብጽ ድርድር ሲያደርጉ የቆዩት የእስራኤል እና የሀማስ ተደራዳሪዎች በመጀመሪያው ምዕራፍ ላይ መስማማታቸው ተሰምቷል።

ሁለቱ ወገኖች ለ3 ቀናት ያደረጉት ውጥረት የተሞላበት ድርድር ጦርነቱን በዘላቂነት ለማስቆም መንገድ የሚጠርግ መሆኑን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ተናግረዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ያቀረበው እና ሁለቱ ተፋላሚ ሀይሎች የተስማሙበት የመጀመሪያ ምዕራፍ የሰላም ስምምነት፤ በሀማስ እጅ የሚገኙ ሁሉም ታጋቾች እንዲለቀቁ እና እስራኤል ከጋዛ ወታደሮቿን እንድታስወጣ የሚጠይቅ ነው።

በአሁኑ ወቅት በሀማስ ስር 48 ታጋቾች የሚገኙ ሲሆን ከነዚህ መካከል 20 የሚሆኑት በሕይወት እንዳሉ ይታመናል።

ስምምነቱን መልካም ጅማሮ እንደሆነ የተናገሩት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ስምምነቱን ለማጽደቅ በዛሬው ዕለት ከካቢኔያቸው ጋር እንደሚመክሩ ይፋ አድርገዋል።

ሀማስ በበኩሉ ጦርነቱ እንዲቆም እና በእስራኤል እጅ የሚገኙ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ለማስለቀቅ እንዲሁም ወደ ጋዛ የሰብአዊ ድጋፍ ያለገደብ እንዲገባ ስምምነቱ ወሳኘ ነው ብሏል።

የእስራኤል ካቢኔ በዛሬው ዕለት በሚኖረው ስብሰባ ስምምነቱን የሚያጸድቅ ከሆነ እስራኤል በ24 ሰዓታት ውስጥ ከጋዛ ወታደሮቿን እንደምታስወጣ ይጠበቃል።

ቀጥሎም ሀማስ በ72 ሰዓታት ውስጥ እስከ ቅዳሜ ድረስ እጁ ላይ የሚገኘ ታጋቾችን መልቀቅ እንደሚጀምር ቢቢሲ ዘግቧል።

የመካከለኛው ምስራቅ እና የምዕራባውያን ሀገራት መሪዎች የሰላም ስምምነቱን አወድሰው በጋዛ የቀጠለውን ሰቆቃ ለማስቆም ከዚህ የተሻለ አማራጭ እና ጊዜ አይኖርም ሲሉ ሁለቱም አካላት ስምምነቱን እንዲያስፈጽሙ ተማጽነዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ባቀረቡት የባለ20 ነጥብ የሰላም ስምምነት ሀሳብ መሰረት የመጀመሪያው ምዕራፍ ስኬታማ የሚሆን ከሆነ፣ ጦርነቱ በዘላቂነት ስለሚቆምበት እና ሀማስ በጋዛ ስለሚኖረው የአስተዳደር ሚና ቀጣይ ውይይቶች የሚደረጉ ይሆናል።

በዳዊት በሪሁን

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review