በጋምቤላ ክልል የዲጂታል አገልግሎትን በማስፋት ለልማት እቅዶች መሳካት በትኩረት እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ

You are currently viewing በጋምቤላ ክልል የዲጂታል አገልግሎትን በማስፋት ለልማት እቅዶች መሳካት በትኩረት እንደሚሰራ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ

AMN መስከረም 29/2018

በጋምቤላ ክልል የዲጂታል አገልግሎትን በማስፋት ለልማት እቅዶች መሳካት በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር በዲጂታል የእቅድ ክትትልና ግምገማ ስርዓት እና በልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደር ዙሪያ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ የምክክር መድረክ እያካሄደ ነው። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ የምክክር መድረኩን ሲከፍቱ እንዳሉት፤ በክልሉ የዲጂታል አገልግሎትን በማስፋት ለልማት እቅዶች መሳካት በትኩረት ይሰራል።

የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዘመናዊና የተሳለጠ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ካለው ፋይዳ በተጨማሪ ስራዎችን ከርቀትና ከየትኛውም ቦታ ሆኖ መምራት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም በክልላዊም ሆነ በሀገራዊ የኢኮኖሚ ግንባታ ሂደት በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሰረቱ የልማት ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችንና ፕሮጀክቶችን ለመቅረጽና ውጤታማነታቸውን ለመከታተል እንዲሁም ለመገምገም የጎላ ፋይዳ አለው ብለዋል።

በመሆኑም የዲጂታል ቴክኖሎጂን በማስፋት የታለመውን የልማትና የብልጽግና ጉዞ ስኬታማ ለማድረግ ተግቶ መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል።

የምክክር መድረኩም በክልሉ ያለውን የመረጃ አያያዝ ስርዓትና በዲጂታል የእቅድ ክትትልና ግምገማ ረገድ የሚስተዋሉ ውስንነቶችን የሚያቃልል መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሯ አመልክተዋል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመከታተልና ስኬታማ ለማድረግ ዘመኑ ያፈራቸውን የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች መጠቀም ያስፈልጋል ብለዋል።

የምክክር መድረኩ ዓላማም የዲጂታል እቅድ ክትትልና ግምገማ ስርዓትን ወደ ክልል በማውረድ የድጋፍና ክትትል ስራዎችን ለማሳለጥ መሆኑን መናገራቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በመድረኩ ላይ በዲጂታል የእቅድ ክትትልና ግምገማ ስርዓት፣ በመንግስት የልማት ፕሮጀክቶች አስተዳደርና አመራር እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ሰነዶች ቀርበው ውይይት እየተደረገባቸው ይገኛል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review