አፍሪካ ከቆሞ ተመልካችነት ተላቃ ወደ ውሳኔ ሰጭነት የምትሸጋገርበትን ጊዜ እውን ለማድረግ በጋራ ዓላማ ልንቀሳቀስ ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በናይሮቢ፣ ኬንያ “ዲጂታላይዜሽንን ለቀጠናዊ የእሴት ሰንሰለት መጎልበት በመጠቀም ለዘላቂ እና አካታች ዕድገት ማዋል” በሚል ጭብጥ እየተካሄደ ባለው 24ኛው የኮሜሳ መሪዎች ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በመድረኩ ባደረጉት ንግግር የሀገራት ዕድገት እና የህዝቦች ግንኙነት እና ብልፅግና እንዴት እንደሚረጋገጥ በመወሰኑ በኩል ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በፍጥነት እያደገ የሚገኘው ቴክኖሎጂ ቀዳሚ ሆኗል ብለዋል።
ጊዜው አፍሪካ ቆማ የምትመለከትበት አይደለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብልጽግና እና ፍትሃዊነት የሰፈነበትን የወደፊት ጊዜ ለመገንባት የሚያስችል ህዝብ፣ ፈጠራ እና የተፈጥሮ ሀብት አለን፤ የሚያስፈልገን ጥረታችንን ማገናኘት እና በጋራ ዓላማ መንቀሳቀስ ብቻ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ይህንን ለማሳካት እንደ ኮሜሳ ያሉ ቀጠናዊ ተቋማት የጋራ ፍላጎትን ወደ ዕድገት መለወጥ እንዲሁም ቅንጅት እና ውህደትን ለማጠናከር ሊንቀሳቀሱ ይገባል ብለዋል።
የዚህ ዓመት ትኩረት በኢኮኖሚ እና በዲጂታላይዜሽን ላይ ማተኮሩ ወቅቱን የጠበቀ ስለመሆኑ አጽንዖት ሰጥተው፤ ዲጂታላይዜሽን የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ ታሪክ እንደገና ለመፃፍ ልዩ ዕድል እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።
ዲጂታል ኢኮኖሚን ማረጋገጥ ዜጎች ክፍያዎችን በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲፈጽሙ፣ አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ እና ድንበር አቋርጠው እንዲገናኙ የሚያስችል የዲጂታል የህዝብ መሠረተ ልማት መገንባትን ያካትታል ነው ያሉት ።
በኢትዮጵያ ይህንን ራዕይ በብሔራዊ ዕቅዳችን “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” በኩል ወደ ተግባር እየቀየርን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ የህዝብ አገልግሎቶችን በዲጂታል መንገድ ተደራሽ በማድረግ እንቅፋቶችንና ቢሮክራሲን አስወግደናል ብለዋል።

የዲጂታል መታወቂያ ፕሮግራም ለመንግስትም ሆነ ለንግድ ስራ መተማመንና ቅልጥፍናን መሰረት እየጣለ እንደሚገኝ እንዲሁም ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ በዲጂታል ክፍያ ስርአት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ግብይቶችን መፈጸሟን ተናግረዋል።
በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እና በብሔራዊ የኮዲንግ ፕሮግራሞች አማካኝነት ደግሞ ከ 2.2 ሚሊዮን በላይ ወጣት ኢትዮጵያውያን ከመጪው ጊዜ ጋር መጓዝ የሚያስችላቸውን ስልጠና እንደወሰዱም አብራርተዋል።
ዲጂታል ፈጠራ ድንበር አያውቅም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ቀጣዩ እርምጃ እነዚህን ብሔራዊ ጥረቶች በቀጣና ደረጃ ማገናኘት መሆን እንደሚኖርበት አሳስበዋል
አክለውም መታወቂያዎች፣ ክፍያዎች እና ዳታዎች ያለችግር የሚፈሱበት፣ ንግድ ደግሞ ያለ ምንም እንቅፋት የሚከናወንበትን የኮሜሳ ቀጠና እውን ለማድረግ ከጎረቤቶቻችን ጋር ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል።
በዳዊት በሪሁን