ኢትዮጵያ የዲጂታል አቅሞች ወደ ሚጨበጡ ውጤቶች ለመቀየር ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ ናት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ

You are currently viewing ኢትዮጵያ የዲጂታል አቅሞች ወደ ሚጨበጡ ውጤቶች ለመቀየር ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ ናት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ

AMN መስከረም 30 /2018

ኢትዮጵያ የዲጂታል ዘርፉን መልከ ብዙ አቅሞች ወደ ሚጨበጡ ውጤቶች በመቀየር የጋራ ብልጽግናን እውን ለማድረግ ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

24ኛው የምስራቅና ደቡብ አፍሪካ አገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) የመሪዎች ጉባኤ ዛሬ በኬንያ ናይሮቢ ተካሄዷል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው ላይ ባደረጉት ንግግር በዓለም ደረጃ ከመቼውም ጊዜ በላይ በፍጥነት እየተለወጠ የመጣው ቴክኖሎጂ የሀገራትን እድገት፣ የማህበረሰብ ትስስር እና የጋራ ብልጽግናን የማረጋገጥ ጉዞን እየወሰነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

አፍሪካ አሁን ቆማ የምታይበት እና የምትጠበቅበት ጊዜ አለመሆኑን ጠቅሰው ፤ ያለውን በርካታ የህዝብ ቁጥር፣ የፈጠራ አቅም እና የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም የበለጸገች እና መጻኢ ጊዜዋ ፍትሃዊ እንዲሆን ለማድረግ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል። ለዚህም ጥረቶቻችንን በማስተሳሰር እና የጋራ ጥቅማችንን ባስጠበቀ መልኩ ርምጃዎችን መውሰድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

እንደ ኮሜሳ ያሉ ቀጣናዊ ተቋማት ያላቸው ፋይዳ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትልቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ የጋራ ፍላጎትን ወደ ተጨበጠ ለውጥ መቀየር ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።

የኮሜሳ የመሪዎች ጉባኤ አጀንዳ የሆነው የዲጂታል መፍትሄዎች ለጠንካራ እና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት ያለው ፋይዳ ወቅቱን የጠበቀ አጀንዳ መሆኑን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት። የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን የአፍሪካ ኢኮኖሚን ታሪክ ዳግም ለመጻፍ ልዩ እድል ይዞ መምጣቱንም አንስተዋል።

ዜጎች ማንነታቸውን መግለጽ የሚችሉበት፣ ደህንነቱ የተጠበቀ ክፍያን መፈጸም፣ አገልግሎቶችን በቀላሉ ማግኘት እና ድንበር ተሻጋሪ ትስስርን ማጠናከር የሚያስችል የዲጂታል መሰረተ ልማት መገንባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የዲጂታል ህልሟን ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችላትን ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ እየተገበረች እንደምትገኝ ገልጸዋል።

ስትራቴጂው በሀገር ደረጃ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ማሳካት የሚያስችል አሻራ ነው ብለዋል። ኢትዮጵያ በ100ዎች የሚቆጠሩ የመንግስት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ማድረጓን ገልጸው፤ ይህም አገልግሎትን ያለ እክል እና የተንዛዛ አሰራር ለማቅረብ ማስቻሉን ነው የተናገሩት።

በዲጂታል ብሄራዊ የመታወቂያ ፕሮግራም አማካኝነት ከ25 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የፋይዳ መታወቂያ ባለቤት መሆናቸውን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም በመንግስት እና በንግድ ተቋማት ተአማኒነት እና ውጤታማነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሰረት መጣሉን አመልክተዋል።

በ2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ የዲጂታል ክፍያ ስርዓት ምህዳር በቢሊዮኖች የሚቆጠር የገንዘብ ግብይት መፈጸሙንም አብራርተዋል። በኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንለጀንስ ኢንስቲትዩት አማካኝነት በብሄራዊ የኮዲንግ ፕሮግራም ወጣት ኢትዮጵያውያን ኢኖቬተር መሆን የሚያስችላቸውን ስልጠና በመውሰድ የብቃት ማረጋገጫ ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ተሞክሮዎች አፍሪካ በክህሎት እና ዲጂታል ፋውንዴሽን ላይ መዋዕለ ንዋይ ካፈሰሰች በዓለም ደረጃ በራሷ መመዘኛዎች ተወዳዳሪ መሆን እንድምትችል ማሳያ ነው ብለዋል።

አሁን ማድረግ ያለብን ብሄራዊ ጥረቶቻችን ከቀጣናዊ አሰራሮች ጋር ማዛመድ እንደሚገባም ነው ያነሱት። ቀጣናዊ ዲጂታል መሰረተ ልማት ኮሜሳን ጨምሮ ቀጣናዊ የንግድ ልውውጥ እና የክፍያ ስርዓት እንዲሳለጥ፣ ኢኖቬሽን ድንበር ተሻጋሪ እንዲሆንና የዲጂታል ተአማኒነትን የማሳደግ አቅም እንዳለው ገልጸዋል።

በዚህ ረገድም ኢትዮጵያ የዲጂታል ራዕይን እውን ለማድረግ፣ የዲጂታል አቅምን ወደ ቀጣናዊ ኃይል ለመቀየር እና አሳታፊነትን ወደ ጋራ ብልጽግና ለማሸጋገር ከጎረቤት ሀገራት ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ ናት ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡ መጪው ጊዜ የሚሸልመው ዛሬ የገነቡትን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዚህም በጋራ እንስራ እንትጋ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review