ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ተጠቃሚ እንድትሆን በጥናት ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለባት ተገለፀ

You are currently viewing ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ተጠቃሚ እንድትሆን በጥናት ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለባት ተገለፀ

AMN – መስከረም 30/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት ተጠቃሚ እንድትሆን በጥናት ላይ የተመሰረተ እና አምራችነት ላይ ያተኮረ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለባት ተገልጿል፡፡

ኢትዮጵያ አምራችነቷን በማሳደግ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በአፍሪካ ገበያዎች በመሸጥ የወጭ ገቢዋን ማሳደግና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብ እንደምትችልም ተጠቁሟል።

የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት፣ የአፍሪካን የእርስ በርስ የንግድ ትስስርን ለማጎልበት የታሪፍ ድንበሮችን በሂደት በማስወገድ አህጉሪቷን ወደ አንድ ገበያ የማምጣት ግብ ያስቀመጠ የአፍሪካ ህብረት ኢንሼቲቭ ነው፡፡

ስምምነቱን ከፈረሙ 54 የአፍሪካ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ ትገኝበታለች። በአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጠና እንደ ሀገር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ለመሆን ሰፊ የዝግጅት ስራዎችም ተሰርተዋል።

ከኤ.ኤም.ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ተመራማሪና በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነት የብሄራዊ ትግበራ ስትራቴጂ ዝግጅት የቴክኒካል ኮሚቴ መሪው ዶክተር አበበ አምባቸው፣ ስምምነቱ ውስጥ መግባት ብቻውን ተጠቃሚ ስለማያደርግ ስትራቴጂ መንደፍና በዘርፉ ያለንን ልምድ ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ የወጭ ንግድ አቅሟ እያደገና ከዘርፉ የምታስገባው የውጭ ምንዛሬ እየጨመረ መጥቷል። እንደ ተመራማሪው ገለፃ የወጭ ንግድ ቢያድግም እንደ ሀገር ከአፍሪካ ጋር ያለው የንግድ ትስስር ግን ዝቅተኛ ሆኖ ይገኛል።

ኢትዮጵያ ከወጭ ንግዷ 14 በመቶውን ብቻ ነው ወደ አፍሪካ ሀገራት ኤክስፖርት የምታደርገው፣ ወደ ሀገር ከምታስገባው ደግሞ 9.6 በመቶው ብቻ ከአፍሪካ ይገባል ያሉት ተመራማሪው፣ የኢንቨስትመንት ትስስሩም ዝቅተኛ መሆኑን በጥናት መረጋገጡን አስገንዝበዋል።

ስምምነቱን ተከትሎ በአፍሪካ የተከፈተውን ነፃ ንግድ ቀጠና በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል ያሉት ተመራማሪው፣ የንግዱ ማህበረሰብ በመረጃና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ መከተል እንደሚገባው ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ በአፍሪካን ገበያዎች ምርት አቅራቢ መሆን የምትችልባቸው በርካታ ዘርፎች እንዳሉም ዶክተር አበባ ጠቁመዋል።

ከግብርና ምርቶች በተጨማሪ የኢንዱስትሪ ምርቶችም ለአፍሪካ ገበያ ለማቅረብ መስራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና ስምምነትን ለመተግበር የሚያስችል ዝርዝር ስትራቴጅ አዘጋጅታ ወደ ተግባር የገባች ሲሆን ተገቢውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማግኘት በየደረጃው የግንዛቤ ማስጨበጥና አምራቾችን የማነቃቃት ተግባራትም ስትሰራ ቆይታ ግብይቱን በይፋ አስጀምራለች።

በይታያል አጥናፉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review