የመዲናዋ ዓሳ አስጋሪዎች

You are currently viewing የመዲናዋ ዓሳ አስጋሪዎች

‎AMN –መስከረም 30 /2018 ዓ/ም

‎ታዳጊ ናሆም ደረሰ እምብርት አዲስ አበባ ተወልዶ ያደገ ሲሆን ዓሳን መብላት እንጂ የማስገር ዕድል ገጥሞት አያውቅም ታዲያ ለመጀመሪያ ግዜ ዓሳ በማስገሩ መደሰቱን ይናገራል ።

‎ከዚህ ቀደም ታዳጊ ናሆም ከወላጆቹ ጋር በመሆን በከተማዋ በሚገኙ የመዝናኛ ቦታዎች እየተዘዋወሩ ይዝናኑ እንደነበር አስታውሶ የዓሳ እርባታ ማዕከሉ ግን ከፍተኛ ደስታ እና ተዝናኖት እንደፈጠረበት ነው የነገረን ።

‎ሌላኛው በዓሳ እርባታ ቦታው ያገኘናቸው አቶ አብርሀም መብራቱ የዊንጌት አከባቢ ነዋሪ ሲሆኑ፤ ቦሌ ቡልቡላ አከባቢ በአዲስ አበባ ከተማ በዓሳ እርባታ ሥራ ላይ የተሰማራ ወጣት እንዳለ ሲሰሙ ለመመልከት በአከባቢው መገኘታቸውን ይገልፃሉ።

‎ከዚህ ቀደም ዓሳን የማስገር ልምድ እንዳላቸው የሚገልጹቱ አቶ አብርሀም፣ ሃይቅ በሌለበት አካባቢ የዓሳ እርባታና እና ዓሳ የሚጠመድባቸው ቦታዎች መገኘት እንዳስደሰታቸው ገልፀዋል።

‎በተለይም እንዲህ ዓይነት ቦታዎች ህፃናት እና ታዳጊዎች አልፎ አልፎ በስልክ እና በኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች አላስፈላጊ ነገሮችን በማየት ጊዜቸውን ከሚያባክኑ፤ በተፈጥሮአዊ ነገሮች እንዲዝናኑ ለማድረግ ዕድል እንደሚሰጥ ተናግረዋል ።

ስለሆነም እንዲህ ያሉ ቦታዎችን በማስፋት ለመዝናናትም ሆነ የስራ ዕድል ከመፍጠር አኳያ ሚናቸው ላቅ ያለ ነው ብለዋል። ‎ልጆቹን ለማዝናናት በቦታው መገኘታቸውን የሚገልጹት አቶ አብርሀም፣ የልጆቹ ደስታ በቃላት የሚገለፅ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል። አቶ አይናለም ሙሉጌታ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 ቦሌ ቡልቡላ ነዋሪ እና የከተማ አርሶ አደር ናቸው ፡፡

አቶ አይናለም የዓሳ እርባታ በመጀመሪያ ጊዜ ሲያከናውኑበት የነበረው ስፍራ ከዚህ ቀደም የመስኖ ስራ ይሠራበት እንደነበር እና ቦታው በበጋ ወራት ውሀው ስለሚተን አቅራቢያው ከሚገኘው ወንዝ ውሀ በመሳብ ከሰበታ የዓሳ ምርምር ማዕከል የዓሳ ጫጩቶችን በመውሰድ 8 ሜትር ጥልቀት ባለው ጉድጓድ ላይ ስራውን መጀመራቸውን ነው ያጫወቱን ።

‎አሁን ላይ ስፍራው የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች እና የውጭ ሃገር ዜጎች ቀልብ በመሳብ ዓሳን ለገበያ ከማቅረብ ባለፈ ዓሳ በማስገር የሚዝናኑበት ቦታ መሆን ችሏል፡፡

‎ለሁለት አመታት ለጎብኚ ክፍት ሳይደርግ ስራውን ሲሰራ መቆየቱን የገለፁት አቶ አይናለም ፡፡ ከዚህ ቀደም ራሳቸው ዓሳ በማስገር በኪሎ ሲሸጡ እንደነበር ገልፀው አሁን ላይ ግን ለህብረተሰቡ ክፍት በማድረግ ጎብኝዎች ራሳቸው ያሰገሩትን ዓሳ ገዝተው እንዲሄዱ የማድረግ ስራም እያከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡

‎ወጣት ያሬድ በአይናለም የዓሳ እርባታ ማዕከል ዓሳ ማስገር እና የማብሰል ስራ የተሰማራ ወጣት ሲሆን በአርባታ ማዕከሉ የስራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ዜጎች አንዱ መሆኑን አጫውቶናል ።

‎አሁን ላይ በእርባታ ማዕከሉ የጥበቃ ስራን ጨምሮ ከ14 ላላነሱ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩን አቶ አይናለም ተናግረዋል።

‎በእርባታ ማዕከሉ ቆረሶ እና ብልጫ የተሰኙ የዓሳ ዝርያዎች የሚረቡ መሆኑንና በሳምንት ሁለት ቀን ቅዳሜና እሁድ ለህዝብ ክፍት እንደሚሆንም ተናግረዋል።

‎በሔለን ተስፋዬ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review