AMN- መስከረም 30/2018 ዓ.ም
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተወዳዳሪነታቸውንና ተመራጭነታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ አስገነዘቡ።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የቁልፍ ተግባራት አፈጻጸም ፊርማ ስነ-ስርዓት ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ(ዶ/ር)፣ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ የዩኒቨርሲቲዎች የቦርድ አመራር አባላትና የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንቶች በተገኙበት ተካሂዷል።
የትምህርት ሚኒሰትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እንደገለጹት፤ ዩኒቨርሲቲዎች በተማሪዎች ተመራጭና ተወዳዳሪ ለመሆን መስራት ይኖርባቸዋል።
ዩንቨርሲቲዎች ለተፈራረሙት የውጤት ስምምነት ውል ተግባራዊነት በቁርጠኝነት መስራትና የልህቀት ማዕከል ለመሆን፣ በየአካባቢያቸው በሚገኙ የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ የትኩረት መስካቸውን ለይተው መስራት አለባቸውም ሲሉ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
በአካባቢያቸው የሚገኙ የማዕድን፣ ቱሪዝምና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ትኩረት አድርገው የትምህርት ፕሮግራማቸውን ለይተው ተወዳዳሪ ሊሆኑ እንደሚገባም ተናግረዋል።
በ2018 የትምህርት ዘመን የዩኒቨርሲቲዎችን ብቃት በትክክል መለየት የሚቻልበት እውቅና የመስጠት ስራ ይጀመራል ብለዋል።

በፊርማ ስነ-ስርዓቱ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ኮራ ጡሹኔ፤ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥና የዘርፉን ችግሮች ለመፍታት በተከናወኑ ተግባራት ለውጦች እየተገኙ መሆኑን ገልጸዋል።
ሆኖም የትምህርት ጥራት ጉዳይ የባለድርሻ አካላትን ርብርብ እንደሚጠይቅና ቀሪ በርካታ ስራዎች ማከናወን እንደሚገባ ተናግረዋል። የሪፎርም ስራዎቹ በተለያዩ ጉዳዮችና ኢንሼቲቮች ተዋቅረው በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ተግባራዊ እንደሚደረጉ ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።