በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ ማናቸውም አይነት የደረቅ እና የፈሳሽ ጭነት ተሽከርካሪዎች እና የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከጉምሩክ ቀረጥ ነጻ ሆነው ወደ ሀገር እንዲገቡ ተፈቀደ

You are currently viewing በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ ማናቸውም አይነት የደረቅ እና የፈሳሽ ጭነት ተሽከርካሪዎች እና የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከጉምሩክ ቀረጥ ነጻ ሆነው ወደ ሀገር እንዲገቡ ተፈቀደ

AMN- መስከረም 30/2018 ዓ.ም

በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ ማናቸውም አይነት የደረቅ እና የፈሳሽ ጭነት ተሽከርካሪዎች እና የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከጉምሩክ ቀረጥ ነጻ ሆነው ወደ ሀገር እንዲገቡ መፈቀዱን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ያላት መሆኑ ቢታውቅም ለዘመናት የዚህ የተፈጥሮ ሃብት ተጠቃሚ ሳትሆን መቆየቷን ገልጿል።

ይህንን ሁኔታ ለመለወጥ መንግስት ሲያደርግ የቆየው እልህ አስጨራሽ ጥረት ተሳክቶ፣ በቅርቡ በካሉብ አካባቢ የሚገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችል ኢንዱስትሪ ተመርቆ የተፈጥሮ ጋዝ የማምረት ስራ በይፋ ተጀምሯል ብሏል።

ይህን ምርት ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ ቤንዚን እና ናፍታ የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን የተፈጥሮ ጋዝ በሚጠቀሙት ተሽከርካሪዎች መተካት አስፈላጊ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

የተፈጥሮ ጋዝ የሚያመነጨው በካይ አየር እጅግ በጣም ዝቅተኛ የሆነ፤ ለተለያየ የሀይል ምንጭ አገልግሎት ሊውል የሚችል፤ በሀይል አጠቃቀም ረገድ ውጤታማነት ያለው ከመሆኑም በላይ በአገራችን የሚመረት በመሆኑ ለነዳጅ ግዥ የምናወጣውን የውጭ ምንዛሪ የሚያስቀር በመሆኑ መንግስት የተፈጥሮ ጋዝ አጠቃቀምን ለማበረታታት መወሰኑን ሚኒስቴሩ ለኤ ኤም ኤን በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡

በዚህም መሰረት ይህ መመሪያ ከወጣበት ቀን መስከረም 30/20018 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ በሙሉ በተፈጥሮ ጋዝ የሚሰሩ ማናቸውም አይነት የደረቅ እና የፈሳሽ ጭነት ተሽከርካሪዎች እና የህዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ከጉምሩክ ቀረጥ ነጻ ሆነው ወደ ሀገር እንዲገቡ መፈቀዱን ገልጿል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review