መዲናዋን በሚመጥን ደረጃ የንግድ ግብይት ሥርዓቱን የማዘመን ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ገልፀዋል፡፡
በከተማው የምርት አቅርቦትና ፍላጐቱ እንዲመጣጠን እና የግብይት ሥርዓቱ የተረጋጋ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ከኤ.ኤም.ኤን አገልጋይ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ 5ቱም በሮች የግብርና ምርቶች መሻጫ ማዕከላት የተገነቡ ሲሆን፤ ከኮሊደር ልማቱ ጋር ተያይዞ የንግዱን መሠረተ ልማት ማሳለጥ የሚችሉ በርካታ ሱቆችና ኘላዛዎች መሠራታቸውን ገልፀዋል፡፡
ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ አምራቹንና ሸማቹን ቀጥታ እንዲገናኝ በማድረግ የደላላ ትስስሩን በማቋረጥ የተረጋጋ የግብይት ሥርዓት እንዲኖር መደረጉንም አንስተዋል፡፡
የቅዳሜ እና የእሁድ ገበያዎች የከተማውን የገበያ ሁኔታ በማረጋጋት ረገድ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑን የቢሮ ኃላፊዋ ገልፀዋል፡፡
የግብርና ምርትና የምግብ ፍጆታ ዕቃዎች በ5 አቅራቢዎች የተጀመረው የቅዳሜ እና እሁድ ገበያ አሁን ላይ 219 አምራቶችና ጅምላ አከፋፋዮች እንደሚሳተፉበትም ተናግረዋል፡፡
ሀገራችን የምትከተለው ነፃ ኢኮኖሚ ቢሆንም ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ሲባል የቅዳሜና የእሁድ ገባያዎች ላይ ከመደበኛ የገበያ ዋጋ 15 በመቶ ቀንሰው እንዲሸጡ መደረጉንም አንስተዋል፡፡
መንግስት የዜጐችን የኑሮ ጫና ለማቃለል የትራፊክ ፍሰቱን ገድቦ በቅዳሜ እና እህድ አስፓልት ላይ ግብይት መፍቀዱ ለገበያው መረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል ነው ያሉት፡፡
የቅዳሜና እሁድ አቅራቢዎች 15 በመቶ ከዋናው ገበያ ቀንሰው የመሸጥ ግዴታ እንዳለባቸው ያነሱት ኃላፊዋ፣ አምራች፣ ጅምላ አከፋፋይና አልፎ አልፎ ቸርቻሪዎች እንደሚሳተፉም ገልፀዋል፡፡
ቸርቻሪዎች 15 በመቶ ቀንሰው መሽጥ ስለማያዋጣቸው እና ትርፋማ ስለማያደርጋቸው 123 ቸርቻሪ ነጋዴዎች ከግብይት ሥርዓቱ እንዲወጡ መደረጉንም ገልፀዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ህግ በማውጣት ህገወጥ፣ መደበኛ የፀና ንግድ ፈቃድ ያላቸው ነጋዴዎች እና ኢመደበኛ ነጋዴዎች በሚል እንዲለዩ መደረጉንም አመላክተዋል፡፡
ኢ-መደበኛ ነጋዲዎችን ወደ ሥርዓት ለማስገባት በሁሉም ክፍለ ከተሞች 1 ሺህ 112 ቦታዎች መለየታቸውን የጠቆሙት ኃላፊዋ፣ የተወሰኑ ክፍለ ከተሞች ወደ ስራ ያስገቡ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ቦታ በማልማት ላይ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
በመዲናዋ አምስቱም መግቢያ በሮች ባሉት የገበያ ማዕከላት የመንገድ ስራ በግንባታ ላይ እንደሚገኝ ገለፀዋል፡፡
የምርት ጥራትና የዋጋ ችግርን በተመለከተ ባለፉት አራት ወራት በተደረገ ቁጥጥር መሻሻል እየታየ ቢሆንም በቀጣይ አሰራሩን የማዘመን ሥራ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የንግድ ፈቃድ እድሳትን በተመለከተም አሰራሩን ሙሉ በሙሉ ዲጂታል የማድረግ ሥራ በመከናወን ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በበረከት ጌታቸው