በመዲናዋ የተከናወኑ የአደባባይ በአላት በስኬት እንዲከበሩ ነዋሪዎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ህብረብሄራዊነትን እና ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ትልቅ መሰረት የሚጥል መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ

You are currently viewing በመዲናዋ የተከናወኑ የአደባባይ በአላት በስኬት እንዲከበሩ ነዋሪዎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ህብረብሄራዊነትን እና ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት ትልቅ መሰረት የሚጥል መሆኑን ነዋሪዎች ገለጹ

AMN- መስከረም 30/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ በተከናወኑ ዓለም አቀፋዊና አህጉር አቀፍ ጉባኤዎችን እንዲሁም ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ክብረ በዓላት የከተማው ነዋሪዎች ያሳዩት አቀባበልና ፍቅር የተሞላበት መስተንግዶ የሚደነቅ እና ቀጣይነት ሊኖረው የሚገባ መሆኑን የመዲናዋ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

በመዲናዋ የኢትዮ-ካሪቢያን ጉባኤ እና 2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፋዊ እና አህጉር አቀፍ ጉባኤዎች እንዲሁም ሃይማኖታዊ እና ባህላዊ ክብረበዓላት ተስተናግደዋል፡፡

በተለይም ብዙ ቁጥር ያለው ህዝብ የሚታደምባቸው ታላላቅ የአደባባይ በዓላት በደማቅ ሁኔታ ተከብረዋል፡፡

ለበዓላቱ በድምቀት መከበር የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንግዶችን በወንድማማችነትና እህትማማመችነት እንዲሁም በእንግዳ ተቀባይነት ያደረጉት ተሳትፎ እና ያሳዩት ፍቅር የሚደነቅ መሆኑን ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር ቆይታ ያደረጉ የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

“ህዝብ መሪውን ይመስላል” የሚለው ወጣት ዘሪሁን ከበደ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የሚያደርጉትን ተምሳሌታዊ ድርጊት በመከተል የከተማዋ ነዋሪዎች ያከናወኑትን ተግባር የሚደነቅና እንግዳ ተቀባይነት ባህላችንን በተግባር ያሳየንበት ነበር ሲል ነው የገለፀው ፡፡

ከመስቀል በዓል ባሻገር በሆረ ፊንፊኔ የኢሬቻ በዓል ላይ ለመታደም ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች እና በአምስቱም የመግቢያ በሮች የመጡ የበዓል ታዳሚዎችን ደግሶ በመቀበል እና በመሸኘት ያሳየው ፍቅር ከመቼውም ጊዜ የተለየ ነው ያለው ወጣቱ፣ ይህም አንዱ የሌላውን ባህል እንደራሱ የመቀበል አስተሳሰቡ ማደጉን ያሳያል ብሏል፡፡

ሌላኛው በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነችዉ ወ/ሮ ሙሉ ደበሌ፣ የከተማዋ ነዋሪዎች ካለፉት ዓመታት በተሻለ መልኩ የአደባባይ በዓላት በስኬት እንዳከናወኑና በተለያየ መንገድ ከጸጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን በዓሉን የጋራ አድርጎ ያሳለፈበት መንገድ ደስ የሚያሰኝ እንደነበር ገልጻለች::

ይህም ህብረተሰቡ ከየትኛውም ጊዜ በላይ ለሰላሙ፣ ለጸጥታውና ለደህንነት ያለው ቅንጅት በእጅጉ ከፍ ያለ መሆኑን እንደሚያመለክት ጠቅሰዋል፡፡

አቶ ተሻገር ደፋሩ በበኩሉ በተከበሩ የአደባባይ በዓላት ላይ ማህበረሰቡ የኢትዮጵያውያን ባህል፣ እሴት፣ ወንድማማችነትና እህትማማችነት በተጨባጭ የታየበት እንደነበር አንስቷል፡፡

የመስቀል ደመራንም ሆነ የኢሬቻ በዓላትን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ በአብሮነት ማክበሩን የገለጹት አቶ ተሻገር፣ ከውጭ ሀገርና ከሀገሪቱ የተለያዩ አቅጣጫዎች ለመጡ እንግዶችም ሲደረግ የነበረው መስተንግዶ ለጸጥታ ኃይሉም ሥራን ያቀለለ እንደነበር አመልክተዋል፡፡

በዓላቱ በስኬት እንዲጠናቀቁ የከተማው ነዋሪዎች ያሳየው ፍቅር የተሞላበት መስተንግዶ የሚደነቅ መሆኑን በማንሳት ይህ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው አስተያየት ሰጭዎቹ ጠቁመዋል፡፡

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review