የታማኝ እጆች አሻራ ያረፈባቸው ህያው ምስክሮች

You are currently viewing የታማኝ እጆች አሻራ ያረፈባቸው ህያው ምስክሮች

በእናንተ ገንዘብ ሀገር እየተሰራች መሆኑን ዳግም በኩራት ልገልጽላችሁ እወዳለሁ

                                                                                                       ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ግብር ዜጎች የተሻለ የኑሮ፣ ጥራትና የተደራጀ የሕይወት ስርዓትን የሚገዙበት የጋራ መዋጮ ስለመሆኑ የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ ግብር የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ ልማት የጀርባ አጥንት እንደሆነም እንደዚሁ። በዘመናዊው የዓለማችን እውነታም መንግስት የህብረተሰብን መሰረታዊ ፍላጎት ለማሟላት መሰረተ ልማትን ማስፋፋት እና የዜጎችን ሁለንተናዊ እድገት ለማፋጠን የሚያስፈልጉ ስራዎችን እንዲያከናውን እና ማህበራዊ ፍትህን እንዲያሰፍን ይጠበቃል፡፡ ለዚህም መንግሥት የገቢ ግብር፣ የተርን ኦቨር ታክስ፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ እና ኤክሳይዝ ታክስ ያሉ የግብር ዓይነቶችን በመጣል ገንዘብ ይሰበስባል።

የግብር ዋነኛ ግብ ደግሞ የመንግሥትን ገቢ ከፍ በማድረግ የዜጎችን የመሰረተ-ልማት ፍላጎት ምላሽ በመስጠት የሀገርን ኢኮኖሚ ማሳደግ ነው። ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት በተከናወነው የ7ኛው ታማኝ ግብር ከፋዮች የእውቅና ሥነ ሥርዓት ላይ የተንፀባረቀውም ይኽው ነው። በ2010 ዓመተ ምህረት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተጀመረው የእውቅና ሥነ ሥርዓት የዜግነት የግብር ግዴታቸውን በወቅቱ እና በታማኝነት የሚፈፅሙ ዜጎችን ለማበረታታት ታቅዶ እየተተገበረ ይገኛል።

በዚሁ መርኃ-ግብር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሚሰበሰበው ግብር በሚታይ መሠረተ ልማት ላይ እንዲውል አድርገናል ሲሉ ተናግረዋል። “ባለፈው ዓመት የምታዋጡት ግብር ለጋራ እድገት እና ለሕዝባዊ ጠቀሜታ በሚውሉ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ላይ እንደሚውል ቃል ገብተን ነበር” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት የሚታየው ለውጥ ለዚያ ቃላችን ሕያው ምስክር ሆኖ ይታያልም ነው ያሉት።

አክለውም “አስታውሱ፤ የዛሬ ጥረታችሁ የነገን ትውልድ የተሻለ መፃኢ እድል እየቀረፀ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “በእናንተ ገንዘብ ሀገር እየተሰራች መሆኑን ዳግም በኩራት ልገልጽላችሁ እወዳለሁ ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በእርግጥም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት በአዲስ አበባ ከተማ በቅርብ ዓመታት ከተጠናቀቁ ወይም ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ አስደናቂ የልማት ስራዎች ለዚህ ምስክር ተደርገው የሚቀርቡ ናቸው፡፡ ከእነዚም መካከል ዋነኞቹ የከተማዋን ገጽታ የቀየሩ፣ የመሰረተ ልማት እና የማህበራዊ አገልግሎት አቅርቦትን ያሻሻሉ ሜጋ ፕሮጀክቶች ህያው ምስክሮች ናቸው።

የአዲስ አበባን ገጽታ ለመቀየር የታቀዱ ሰፊ የከተማ እድሳት ፕሮጀክቶች ውስጥ የሚካተተው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ዋነኛው ነው፡፡ በተለያየ ምዕራፍ ተከፋፍሎ የተከናወነው ይህ ፕሮጀክት የመዲናዋን ዋና ዋና መንገዶች ያካተተ ሲሆን፣ ፒያሳ-4 ኪሎ፣ ሜክሲኮ-ሳር ቤት እና ቦሌ ኤርፖርት-መገናኛ- 4 ኪሎ ኮሪደሮች በዋናነት ይጠቀሳሉ። እነዚህ ልማቶች መንገዶችን ከማስፋት ባሻገር የእግረኛ መንገዶችን፣ የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎችን፣ የትራንስፖርት ተርሚናሎችን እና የህፃናት መጫወቻ ስፍራዎችን ያካተቱ ናቸው።

ከተማዋን ለነዋሪዎች ምቹና ለቱሪስቶች ማራኪ ካደረጉ የልማት ስራዎች መካከል የዓድዋ ድል መታሰቢያ ሌላኛው ነው፡፡ በከተማዋ እምብርት ላይ የተገነባው ይህ ግዙፍ መታሰቢያ የኢትዮጵያን ታሪክና የዓድዋ ድልን ከማሳየቱ ጎን ለጎን በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ዘመናዊ ሙዚየም እና የሕዝብ መሰብሰቢያ ስፍራ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። የወንዝ ዳርቻዎችን ያጸዳው ይህ የልማት ፕሮጀክት፣ የእግረኛ መንገዶች፣ የብስክሌት መንገዶች፣ ፓርኮች እና አረንጓዴ የለበሱ ውብ ስፍራዎች አፍ አውጥተው የሚመሰክሩት ሀቅ የተሰበሰበው ግብር ምን ላይ እንደዋለ ነው።

በ2017 በጀት ዓመት ብቻ ግንባታቸው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት የበቁትን የመዲናዋን የልማት ፕሮጀክቶች ለማሳያ ያህል ጨምረን እንመልከት፡፡ በበጀት ዓመቱ 15 ሺህ 960 ፕሮጀክቶች ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉ ሲሆን፣ ፕሮጀክቶቹ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸው የጎላ ስለመሆኑ ይገለጻል፡፡ ለግንባታቸውም ከ95 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 91 ቢሊዮን ብር በመንግስት እና 4 ቢሊዮን ብር በህብረተሰቡ ተሳትፎ የተሸፈነ ስለመሆኑ የአዲስ አበባ ከተማ ዲዛይንና ግንባታ ስራዎች ቢሮ መረጃ ያሳያል፡፡

የቤቶች ግንባታ፣ የንግድና የኢንዱስትሪ ማዕከላት፣ የህፃናት መጫወቻ ስፍራዎችና ከላይ የተገለፁት ፕሮጀክቶች በአንድ በኩል የከተማዋን ውበትና ምቾት ሲያሻሽሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በትራንስፖርትና በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ አዎንታዊ ተጽዕኖ ማሳየታቸው ተረጋግጧል፡፡ ለዚህም የሀገር ወዳድ ታማኝ ግብር ከፋዮች አሻራ በጉልህ የሚጠቀስ ሰለመሆኑ በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት መምህሩ ደገሌ ኢርገኖ (ዶ/ር) ያስረዳሉ፡፡

በታማኝ ግብር ከፋዮች ከፍተኛ ገቢ በማመንጨት እና ከዚህ ገቢ ጋር ተያይዞ ግልፅነትና ተጠያቂነትን በማረጋገጥ በልማት የተለወጡ ሀገራትን ለአብነት እንጥቀስ። ለዚህም እንደ ኖርዌይ፣ ስዊድን እና ዴንማርክ ያሉ ሀገራት ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ሀገራት ከፍተኛ የግብር ገቢ በመሰብሰብ ለጤና፣ ለትምህርት፣ ለሕፃናት እንክብካቤ እና ለጡረታ አጠቃላይ የህዝብ አገልግሎቶችን ይሰጣሉ። ዜጎች ግብራቸው በግልፅነት እና በብቃት ጥቅም ላይ እንደሚውል መተማመን አላቸው። ይህ መተማመን ከፍተኛ የሥነ-ምግባር ግዴታን ይፈጥራል፤ ይህም ሰዎች ግብርን በፈቃደኝነት እንዲከፍሉ ያደርጋል።

ወደ አህጉረ አፍሪካ መለስ ስንልም በቅርብ ጊዜያት በግብር አሰባሰብ እና በገቢ ቅስቀሳ ላይ አስደናቂ ለውጥ ካመጡ የአፍሪካ ሀገራት አንዷ የሆነችውን ሩዋንዳ እናገኛለን። በሩዋንዳ የግብር አስተዳደሩን ግልጽ እና ቀልጣፋ በማድረግ በዜጎችና በመንግሥት መካከል ያለውን መተማመን አሳድገዋል። የግብር ገቢ በሀገሪቱ ልማት ላይ ያለውን ተጨባጭ አስተዋፅኦ ለዜጎች በግልጽ ማሳየት ችለዋል። ግብር ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት (Tax-to-GDP ratio) ምጣኔያቸው በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር አድርጓል። ይህ የገንዘብ መጠን ትምህርት፣ ጤና እና መሠረተ ልማቶችን ለማጠናከር ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

የጆሃንስበርግ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪና ‘REWARDING TAX COMPLIANCE: TAXPAYERS’ ATTITUDES AND BELIEFS’ ጥናታዊ ጽሑፍ አዘጋጇ ማሪና ቦርማንም በጥናታቸው እንዳመላከቱት የግብር ስርዓቱ ፍትሐዊ እንደሆነ እና ሁሉም ሰው በተመጣጣኝ ድርሻ እንደሚከፍል ሲታመን የመንግሥት አገልግሎቶች ጥራት ከፍ ይላል፡፡ የተሰበሰበው ገንዘብም በግልጽና በብቃት ለሕዝብ ጥቅም እንደሚውል ሲረጋገጥ እና  የግብር አከፋፈል ሂደት ቀላል እና ያልተወሳሰበ ሲሆን ውጤታማ የግብር አሰባሰብ እንዲኖር ያስችላል ይላሉ፡፡

አያይዘውም የታማኝ ግብር ከፋይነትን ለማሳደግ ከባህላዊ የቅጣትና የቁጥጥር ሥርዓቶች ባሻገር ሰፊ ምክሮችን ይሰጣሉ። ዋናው ግብ ግብር መክፈልን ከቅጣት ፍራቻ ወደ ሥነ-ምግባራዊና ማኅበራዊ ግዴታ መለወጥ ነው። ግብር ሰብሳቢው አካል የገንዘቡን ጥቅም በግልጽ ማሳየት አለበት። ዜጎች ግብራቸው ለትምህርት ቤቶች፣ ለሆስፒታሎች፣ ለመንገዶችና ለሚታዩ ማህበራዊ ፕሮጀክቶች በአግባቡ እየዋለ መሆኑን ሲያዩ፣ በፈቃደኝነት የመክፈል ፍላጎታቸው እንደሚጨምር ያብራራሉ።

የመንግሥት ተጠያቂነትንና ግልጽነትን ማረጋገጥ ወሳኝ ስለመሆኑ የሚጠቅሱት የደቡብ አፍሪካው ሮድስ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዋ ፕሮፌሰር ሊላ ስቶክ በበኩላቸው፣ የግብር አከፋፈልን ሂደት ቀላልና ቀልጣፋ ማድረግ የዜጎችን የማሟላት ወጪ (Compliance Cost) ይቀንሳል፤ ይህም ለታማኝነት ማደግ ያግዛል ባይ ናቸው። ከመጠን በላይ የተወሳሰበ የግብር ሥርዓት ታማኝነትን ይቀንሳል፤ ብዙ ጊዜን ይወስዳል፤ የሙስና አደጋን ይጨምራል፤ የግብር ሥርዓቱን ማቅለል፣ ውስብስብ የግብር ሕጎችንና አሠራሮችን መቀነስ እንደሚገባም ይመክራሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሙስናን እና ሌብነትን ለማስወገድ በምናደርገው ጥረት ሥርዓቶቻችንን ማጠናከራችንን እንቀጥላለን። ግብር ከፋዮችም በመሰል ጎጂ ተግባር የተሠማሩ ሰዎችን ባለመተባበር እንዲያግዙ አሳስባለሁ ማለታቸው ለዚሁ ነው።

ከባህሪ ሳይንስ (Behavioral Science) ባለሙያዎች አንጻር ጉዳዩን ካየነውም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዋን ሀሳብ የሚያጠናክር ሆኖ እናገኘዋለን። እንደ ባለሙያዎች አስተያየት ከሆነም ምንም እንኳን ቁጥጥርና ቅጣት አስፈላጊ ቢሆንም እሱ ብቻውን ውጤታማ ላይሆን ወይም መተማመንን ሊያሳጣ ስለሚችል ታማኝ ከፋዮችን ማመስገን ወይም ማበረታታት እንደ አማራጭ ዘዴ ይመክራሉ። እንደዚሁም ዜጎች የግብር ሥርዓቱን እንዲረዱት እና ግብር የመክፈል ማህበራዊ ጥቅሙን እንዲያውቁ ትምህርታዊ ዘመቻዎችን በቋሚነት ማካሄድ እንደሚገባ ያሳስባሉ።

የ2017 በጀት ዓመት 7ኛው የታማኝ ግብር ከፋዮች ዕውቅና እና ሽልማት መርኃ ግብር በተገባደደው ሳምንት ተከናውኖ 105 ግብር ከፋዮች በፕላቲየም ደረጃ፤ 245 በወርቅ ደረጃ እንዲሁም 350 ግብር ከፋዮች በድምሩ 700 ግብር ከፋዮች እውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። በተጨማሪም ባለፉት አራት ዓመታት የግብር ከፋዮች እውቅና በተከታታይ የፕላቲኒየም ተሸላሚ የሆኑ 30 ግብር ከፋዮች ልዩ ተሸላሚዎች ሰለመሆናቸው በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

በሽልማት መርኃ ግብሩ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መንግሥት ኢትዮጵያ መቀየር አለባት፣ መበልጸግ አለባት ብሎ በቁርጠኝነት አምኖ እየተጋ ይገኛል ሲሉ አስገንዝበዋል። ይህ ትጋቱ ሊሳካ የሚችለውም በምን እንደሆነ ባብራሩበት ንግግራቸው የግሉ ሴክተር ከትርፍ በላይ ማህበራዊ ዓላማን ያነገበ ሥራ የእያንዳንዱ ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎች እና ባለቤቶች አንዱ ዋነኛ ተልዕኮ መሆን እንዳለበት አስረድተዋል።

“የምንሠራው ለእኛ ብቻ ሳይሆን፤ ለትውልድ ጭምር ነው የሚለውን አምናችሁ እና ከልብ ተቀብላችሁ የምትተገብሩ መሆን ይጠበቅባችኋል” ሲሉም አስገንዝበዋል። በእርግጥም ግብርን አስመልክቶ የተሰሩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ታማኝ ግብር ከፋይነት ከገንዘብ መሰብሰብ ባሻገር በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለውን ማህበራዊ ውል የሚያጠናክር ቁልፍ የልማት ምሰሶ ሆኖ እናገኘዋለን።

በሳህሉ ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review