- የባህር በር ለኢትዮጵያ የደህንነት እና የልማት መረጋገጥ ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ለስኬታማነቱ ሁሉም መተባበር እንዳለበት ተመላከልቷል
የዓለም ንግድ ድርጅት እ.ኤ.አ በ2021 ይፋ ያደረገው መረጃ በዓለም 44 ወደብ አልባ ሀገራት መኖራቸውን ያትታል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 31 ያህሉ ደሃ ናቸው፡፡ 13ቱ ደግሞ ከድህነትም በታች ሲሆኑ መገኛቸውም አፍሪካ ናት፡፡ ቦትስዋና፣ ቡሩንዲ፣ መካከለኛው አፍሪካ፣ ቻድ፣ ሌስቶ፣ ማላዊ፣ ማሊ፣ ኒጀር፣ ዚምባቡዌ፣ ሩዋንዳ፣ ስዋዝላድ፣ ኡጋንዳ፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ዛምቢያ፣ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን የባህር በር ከሌላቸው የአፍሪካ ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ዣን ፖል ሮድሪግ እ.ኤ.አ በ2020 “The Geography of Transport Systems” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መፅሐፍ የባህር በር ባለቤት መሆን ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ዕድገት እጅግ ወሳኝ ጉዳይ መሆኑን ያብራራሉ፡፡ ዓለም ላይ ያሉ ባለከፍተኛ ኢኮኖሚ ሀገራት የወደብ ባለቤቶች ናቸው፡፡
እነ አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና፣ ጃፓንና ብዙዎቹ የአውሮፓና የላቲን አሜሪካ ሀገራት ለኢኮኖሚ ጥንካሬያቸው ብቻ ሳይሆን ለደኅንነታቸውም ቢሆን ወሳኝ ሀብት የባህር በር ስለመሆኑም ጠቁመዋል፡፡
ታድያ የባህር በር አልባ መሆን ከባድ ችግር የሚያስከትል መሆኑም ተመላክቷል፡፡ በመሆኑም አንዳንድ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በስትራቴጂክ ወዳጅነት እና በዲፕሎማሲያዊ ጥረት ችግሮቻቸውን ማቃለል ችለዋል፡፡ ይህ ጉዳይ በህግ ማዕቀፍም የሚደገፍ ነው። ለአብነትም በአፍሪካ ህብረት ቻርተር መግቢያ ላይ እንደሰፈረው የአፍሪካ ሀገራት የባህር በር የሌላቸው ሀገራት በባህር ላይ የመጠቀም መብታቸው እንዲጠበቅ እውቅና ይሰጣል፡፡
በቻርተሩ ላይ በሰፈረው መረጃ መሰረት በአፍሪካ በርካታ የባህር በር የሌላቸው ሀገራት አሉ፡፡ ሀገራቱ ምንም እንኳን ብዙ የተፈጥሮ ሃብቶች ቢኖሯቸውም የዓለምን የባህር ንግድ ስርዓት ሙሉ በሙሉ ማግኘት ባለመቻላቸው ለተለያዩ ኪሳራዎች ይጋለጣሉ፡፡ በመሆኑም የባህር በር የሌላቸው ሀገራት የባህር በር ካላቸው ሀገራት መጠቀም የሚችሉበትን መርሆ ከዓለም አቀፍ ሕግጋት ጋር በማመሳከር ቻርተሩ በመርህ ደረጃ አስቀምጧል፡፡
ኢትዮጵያም በተሳሳተ መንገድ ከሶስት አስርት ዓመታት በፊት ከእጇ የወጣውን የባህር በር ባለቤትነት መልሳ ለማግኘት በሰላማዊ መንገድ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ጥረቷ መልካም ውጤት እያስገኘላት ስለመሆኑ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በሕዝብ ተወካዮች እና ፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የ5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ላይ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
የባህር በር ጉዳይን ዓለም አቀፍ የመነጋገሪያ ሐሳብ ማድረግ ተችሏል ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ በቀጣይነት የቀጣናችንን የጋራ የመልማት ፍላጎት ያገናዘበ ትብብርና ትስስርን ለማጠናከር ዲፕሎማሲያዊና ሰላማዊ ጥረቶች ይደረጋሉም ብለዋል፡፡
አክለውም፣ መንግሥት ፍትሐዊና አስተማማኝ የባህር በር ለማግኘት ከቀጣናው ሀገራት ጋር በዲፕሎማሲያዊና በሰላማዊ መንገድ ይሰራል ሲሉም ገልጸዋል። ለመሆኑ የባህር በር ጉዳይ መሬት እንዲይዝ ከማን ምን ይጠበቃል? በተለይ ህዝቡ፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ፣ ዲያስፖራው እና መንግስት በምን ልክ ሊሰሩ ይገባል? ስንል ከፖለቲካል ሳይንስ፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ከታሪክ ምሁራን ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡
በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉጌታ አስፋው በአሁኑ ጊዜ የባህር በር ጉዳይ መነሳቱ ወቅቱን የጠበቀ ነው ብለው፣ ጥያቄው እልባት እንዲያገኝ መላው ኢትዮጵያዊ በየፊናው መስራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ መንግስት እያደረገ ያለው ጠንካራ ጥረት በምሁራን፣ በዲያስፖራውና በዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ከተደገፈ ተፈላጊው ውጤት ይገኛልም ብለዋል፡፡
የባህር በር ጉዳይ ወሳኝ መሆኑን የገለፁት መምህሩ፣ የባህር በር ያለመኖር ጉዳይ በኢኮኖሚ ላይ ብዙ ተፅዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ የባህር በር አግኝቶ የተሻለ አቅም መገንባት ሀገር በሁለንተናዊ መልኩ የተረጋጋች እንድትሆን ያደርጋል። ስለሆነም እንደ ሀገር በሙሉ ልብ ልንሰራበት ይገባልም ሲሉ መክረዋል፡፡

ይህ ሃሳብ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አቋምንም ያጠናክረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም ከመላው ኢትዮጵያ ከተውጣጡ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ጋር በተወያዩበት ወቅት በዚሁ ጉዳይ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፣ “እንደ ሀገር ያለን ፅኑ አቋም የባህር በር የፖለቲካ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጥያቄ መሆኑ ነው” ማለታቸው አይዘነጋም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ የሁልጊዜም ፍላጎት ከጎረቤቶቿ ጋር በጋራ መልማት መሆኑንም በውይይቱ አንስተው፣ ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር እና ከፍተኛ የህዝብ ብዛት ያላት እንደመሆኗ ሰላም እና ልማት ቁልፍ ጉዳዮች እንደሆኑ ጎረቤቶቿ ሊረዱ እንደሚገባ አመልክተዋል። የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ በህጋዊ እና ሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኝ እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቁመው፣ የባህር በር አለመኖር በኢኮኖሚዋ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ እንደሚገኝ ገልጸው ነበር፡፡
ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ በሁለቱ ምክር ቤቶች የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ባስተላለፉት መልዕክትም፣ ኢትዮጵያ ከዓባይና ከቀይ ባህር መካከል የምትገኝ ሀገር ነች፤ እጣ ፈንታዋና መፃዒ እድሏም ከሁለቱ ውሃዎች ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ፍትህን ባልተከተለ መንገድና ሕዝብን ባላማከለና ባላሳተፈ አግባብ ተገልላ መቆየቷን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ወደነዚህ ውሃዎች እንድትመለስና ፍትሐዊ የልማት ተጠቃሚ እንድትሆን መንግሥት በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ሀገራችን በድንበር ተሻጋሪ ሀብቶቿ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ስትቀበል በዚያው ልክም አስተማማኝ የባህር በር የማግኘት መብቷን ማረጋገጥ ይኖርባታል ብለዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያ ህልውና መሰረት በሆኑት በሁለቱ ታላላቅ የውሃ ሀብቶች ዙሪያ መንግሥት ያልተቋረጠ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ይገኛል ያሉ ሲሆን፣ እስከ አሁን በተደረጉ ጥረቶች አስተማማኝና ዘላቂነት ያለው የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ ከፍ ወዳለ ደረጃ የተሸጋገረና ይህ ፍትሐዊ ጥያቄም በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዘንድ እያደገ የመጣ ቅቡልነት ማግኘት መቻሉን አብራርተዋል።
የታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰርየታሪክ ተመራማሪው ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራት በሳል ዲፕሎማሲያዊ አካሄዶችን መከተል እና ያሉትን ሰላማዊ አማራጮች ሁሉ አሟጥጦ ለመጠቀም የሚደረገው የመንግስት ጥረት መልካም መሆኑን ጠቅሰው፣ የባህር በር ለኢትዮጵያ የደህንነት እና የልማት ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ለስኬታማነቱ ሁሉም መተባበር እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡
ረዳት ፕሮፌሰር አደም እንደሚሉት፣ ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ ታሪክ ያላት ሀገር ነች፡፡ በዓለም ላይም በስልጣኔዋም ሆነ በታሪኳ ትልቅ ክብር አላት፡፡ ይህም ክብርና ታላቅነት ከቀይ ባህር ጋር ባላት አቀማመጥ አሊያም ቅርበት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከቀይ ባህር ቅርብ በሆነችበት ጊዜ ለቅኝ ገዢዎች ያልተጋለጠች ገናና ሀገር ናት። በዚህም የጥቁሮችን መብት ያስከበረች በመሆኗ በፖለቲካዊ፣ በማህበራዊም ሆነ በኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ጠንካራ ሆና ዘልቃለች፡፡
የኢትዮጵያ መርከቦች ቀይ ባህርን አቋርጠው ወደ በርካታ የዓለማችን አካባቢዎች ይንቀሳቀሱ እንደነበር የጠቀሱት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ የባህር በር ባለቤት በነበርንበት ዘመን በብዙ መልኩ ጠንካራ ሀገር ነበረን ብለዋል፡፡

በዘመነ ኢህአዴግ የባህር በራችንን አጥተናል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ይህም ሰፊ የሆነ መነሻ ታሪክ እንዳለው ገልፀዋል። ዞሮ ዞሮ የባህር በር ለኢትዮጵያ ክብሯ፣ ትርፏ፣ ኃያልነቷ፣ የበለፀገችና ዋጋ ያላት ሀገር የመሆኗ ምስጢር ነበር፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ ሰላማዊ በሆነ ዲፕሎማሲያዊ መንገድ ለኢትዮጵያውያንም ለጎረቤት ሀገራትም በሚጠቅም መልኩ ብንወያይና መፍትሔ ብናበጅለት ትልቅ አማራጭ ነውም ብለዋል፡፡
እንደ ሀገርም በጋራ ድርድርና ውይይት የህዳሴ ግድቡን ግንባታ እንዳሳካን የባህር በሩንም ጉዳይ በምክክር፣ በውይይትና በሰላማዊ መንገድ መፍትሔ ብንፈልግለት ለሁላችንም ብዙ ጥቅም ይኖረዋል ብለዋል ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል። ለዚህ ደግሞ ጠንካራ ዲፕሎማቶችን በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት መመደብ ያስፈጋል፡፡ የኃይማኖት ድርጅቶችም ለዚህ ትልቅ ሚና መጫዎት ይኖርባቸዋል ሲሉ አክለዋል፡፡
የባህር በር ጥያቄ አሊያም ሀሳብ አሁን መነሳቱ በትክክልም ወቅታዊነቱን የጠበቀ መሆኑን የገለፁት ረዳት ፕሮፌሰር አደም፣ የኢትዮጵያ መረጋጋትና ሰላም መሆን ለቀጣናው ሀገራት መረጋጋትን የሚፈጥር ሲሆን፣ በአንፃሩ ኢትዮጵያ ላይ በፖለቲካ፣ በወታደራዊ፣ በኢኮኖሚም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች የሚፈጠረው ችግር ለአካባቢው ሰላም አይሰጥም፡፡ በመሆኑም ሀገራት ይህንን በውል መገንዘብ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
መምህር ሙሉጌታ በበኩላቸው፣ የባህር በር የማግኘት ጉዳይ የኢትዮጵያ ህዝብ ብሔራዊ ጥቅም ነው፤ ሁሉም የሚሳተፍበት ጉዳይ መሆን አለበት ብለው፣ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተዋጽኦ ማድረግ የማይችል አካል መኖር የለበትም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያን በተለያዩ የዓለም መድረኮች ላይ የሚወክሉ አካላት በተጠና፣ በተደራጀ እና በተናበበ መልኩ የጋራ የሆነ አቋም በመያዝ በዚህ ጉዳይ ላይ በጋራ መስራት እንዳለባቸው የመከሩት መምህሩ፣ ከዚህ ባለፈም የባህር በር ፍላጎትን ለማሳካት ከስትራቴጂክ አጋሮች ጋር በተናበበ መንገድ መስራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡ ይህም ዲፕሎማሲን በዳበረ እና በተደራጀ መንገድ በመተግበር በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ጫና መፍጠርን ያካትታል ብለው፣ በተለይም በፀጥታው ምክር ቤት ተሰሚነት ያላቸው ሀገራት እንዲደግፉን በርትቶ መስራት እንደሚገባ መክረዋል፡፡
በይግለጡ ጓዴ