በኮሪደር ልማቱ ምክንያት የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ደምቀዋል፡፡ ውብ፣ ማራኪና ሰፋፊ አረንጓዴ የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች፣ የህፃናት መጫወቻዎች ተገንብተዋል፤ እነዚህም የከተማዋን ገፅታ ለውጠዋል። በተጨማሪም፣ የአውቶብስና የታክሲ ተርሚናሎች፣ የምድር ውስጥ ፓርኪንግ፣ የታክሲ ማውረጃና መጫኛ ቦታዎች፣ የመሮጫ ትራኮች፣ የእግረኛ መንገዶች፣ የብስክሌት መንገድ፣ የእግረኛ መሸጋገሪያ ድልድዮች የከተማዋን መልክ ከመቀየራቸውም ባሻገር የትራፊክ ፍሰቱን አቀላጥፈዋል፤ የትራንስፖርት አገልግሎትንም አዘምነዋል፡፡
በኮሪደር ልማቱ የተሰሩት የመሰረተ ልማቶች ለከተማዋ ነዋሪዎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የስራ ዕድል ፈጥረዋል። በተለይም በከተማዋ የተሰሩ መናፈሻዎች፣ ፋውንቴኖች፣ ፕላዛዎች፣ እግረኛ መንገዶች ከመዝናኛነት ባለፈ ለነዋሪዎቹ የገቢ ምንጭ እያስገኙ ነው፤ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ጋር ቆይታ ያደረጉ የፎቶ ካሜራ ባለሙያዎች አሰተያየትም ይህንኑ ያረጋግጣል፡፡
የመስቀል በዓልን ጨምሮ ሌሎች የአደባባይ በዓላትን ለማክበር የሚወጡ ታዳሚያንን ፎቶ የሚያነሱ ባለሙያዎች የኮሪደር ልማቱ ያስገኘላቸው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ቀላል ግምት የሚሰጠው አለመሆኑን ነግረውናል፡፡
በአራት ኪሎ ፕላዛ ላይ እና አካባቢው ፎቶ ግራፍ በማንሳት የሚተዳደረው ወጣት መኮንን ሲሳይ የኮሪደር ልማቱ ለእሱና ለጓደኞቹ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይዞለት የመጣ መሆኑን ይገልጻል፡፡ ከዓመታት በፊት በ500 ብር ወርሃዊ ደመወዝ ተቀጥሮ ፎቶ ግራፍ የማንሳት ስራውን የጀመረው ወጣት መኮንን አሁን፣ በ100 ሺህ ብር ዘመናዊ ካሜራ በመግዛት በአራት ኪሎ ፕላዛ አካባቢ ፎቶ ግራፍ በማንሳት ህይወቱን እየመራ ይገኛል፡፡
ወጣት መኮንን ባጋራን ሀሳብ፣ ከዚህ ቀደም ሸራተን ሆቴል አካባቢ ፎቶ ሲያነሳ እንደነበር ገልጾ፣ አሁን ከአራት ኪሎ ፕላዛ እስከ ፒያሳ ድረስ ባለው መንገድ ነዋሪዎችን ፎቶ በማንሳት ከፍተኛ ገቢ እያገኘ ነው፡፡ መኮንን እና ጓደኞቹ በአዲስ አበባ ፓርኮች አስተዳደር ስምንት ወጣቶች በመሆን “ሙሴ እና ኦሊያድ ጓደኞቻቸው” በሚል ስያሜ በማህበር ተደራጅተው በኮሪደር ልማት የለሙ አካባቢዎች ላይ ፎቶ ግራፍ ያነሳሉ፡፡
የኮሪደር ልማት ከስሞ የነበረውን የመስክ ፎቶ ስራ ዳግም ነፍስ እንዲዘራ አድርጎታል የሚለው ወጣት መኮንን፣ አሁን
ከ10 ሺህ ብር በላይ ወርሃዊ ገቢ እንደሚያገኝ እና በዚህም ቤተሰቦቹን እና ወላጆቹን እንደሚያስተዳደር ገልጿል፡፡
በኮሪደር ልማት በተሰራው የመናፈሻ ቦታ ላይ በፍጥነት እና በጥራት ፎቶ ግራፎችን በማንሳት ለተነሺዎች በሶፍት ኮፒ የሚሰጠው መኮንን፣ የኮሪደር ልማቱ ከመዝናኛነት ባለፈ ለእሱ እና ለጓደኞቹ የገቢ ምንጭ እንደፈጠረላቸው ይናገራል። ለእይታ ማራኪ የሆነች ከተማ ለነዋሪዎች ደስታ ከመፍጠር እና ከመዝናኛነት ባለፈ ነዋሪዎቹን ፎቶ ግራፍ በማንሳት ለቀጣይ ትውልድ አሻራ እንዲሆን ቅርሳቸውን ያስቀመጣሉ፡፡
ነዋሪዎች በተሰሩ የመናፈሻ ቦታዎች እና ፋውንቴኖች ላይ ፎቶ ሲነሱ የፎቶ አንሺዎች ገቢ እንደሚጨምር ወጣቱ ሃሳቡን ያጋራል፡፡ ከአሁን በፊት ስራ የሌላቸው ወጣቶች በተሰራው የኮሪደር ልማት ፎቶ በማንሳት ተደራጅተው የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡
በፊት ተቀጥሮ ይሰራ የነበረው የፎቶ ግራፍ ባለሙያ መኮንን አሁን ለራሱ በመስራት ገቢውን ማሳደግ ችሏል። የከተማ ውበት ሲጨምር ለነዋሪዎች ከእይታ ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚሰጥ መሆኑን ወጣቱ ያስረዳል፡፡ አሁን በየቦታው እና በየመንገዱ ዳር ፎቶ ግራፍ ለማንሳት አካባቢው ምቹ ሆኗል። ሰዎችም ፎቶ የመነሳት ባህላቸው ከበፊቱ እንደጨመረ ትዝብቱን ይናገራል፡፡
ስራውን በደስታ፣ በትጋት እና በፈገግታ የሚሰራው መኮንን፣ እንደ አሸንዳ፣ ሻደይ፣ ኢሬቻ፣ የመስቀል እና ጥምቀትን ጨምሮ ሌሎች የአደባባይ በዓላትን ለማክበር ወደ ጎዳና የሚወጡ ሰዎችን ፎቶ ግራፍ ያነሳል። በእነዚህ ወቅት ወጣቶቹ እና ሴቶች በቡድን በመሆን ፎቶ ግራፍ የመነሳት ፍላጎታቸው ከፍተኛ መሆኑን ወጣት መኮንን ይገልጻል፡፡ የተማሪዎች ምረቃት እና የልደት ፕሮግራም ሲኖርም ፎቶ በማንሳት ገቢውን እንደሚጨምር ይናገራል፡፡
ወጣት ዳንኤል አበበ የካሜራ ባለሙያ ነው፡፡ በተሰራው የኮሪደር ልማት ላይ እንደ ወጣት መኮንን ፎቶ ግራፍ በማንሳት የተሻለ ገቢ እያገኘ መሆኑን ይናገራል፡፡ ከሁለት ዓመት ወዲህ ወደ ስራ የገባው ወጣቱ በጎዳናዎች ላይ በመዘዋወር ነዋሪዎችን ፎቶ ግራፍ ያነሳል፡፡ በፊት ተቀጥሮ ይሰራ እንደነበር ገልጾ፣ አሁን ግን በራሱ ካሜራ ፎቶ በማንሳት የተሻለ ገቢ ማግኘት ችሏል፡፡
የአደባባይ በዓላት ሲመጡ የተሻለ ገቢ እንደሚያገኝ ገልጾ፣ እንደ መስቀል፣ ኢሬቻ፣ ጥምቀት እና የመሳሰሉት የአደባባይ በዓላት ላይ የነዋሪዎች ፎቶ የመነሳት ፍላጎት ይጨምራል፡፡ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችንም ፎቶ ግራፍ እንደሚያነሳ ወጣት ዳንኤል ገልጾ፣ በዚህም ገቢው እንደጨመረ ይጠቁማል።
በወር 4 ሺህ ብር ተቀጥሮ ሲሰራ የነበረው ወጣት ዳንኤል አሁን በራሱ መስራት ሲጀምር በወር ከ10 ሺህ ብር በላይ እንደሚያገኝ ተናግሯል፡፡ በከተማዋ መናፈሻዎች፣ ፋውንቴኖች፣ ፕላዛዎች ሲሰሩ ለነዋሪዎች ከመዝናኛነት ያለፈ ጠቀሜታ የሚሰጡ መሆኑን ወጣት ዳንኤል ገልጾ፣ ሰው ለመዝናናት በሚወጣበት ጊዜ የከተማዋን ውበት በፎቶ ካሜራ በማንሳት ለቀጣዩ ትውልድ አሻራቸውን እያስቀመጡ ነው። የሚያነሱት ፎቶ ለነዋሪዎቹ ማስታወሻ ለእነሱም ደግሞ የገቢ ምንጭ የሆናቸው መሆኑን ባለሙያው ይናገራል፡፡
ወጣት ሀብታሙ ተስፋዬ በአራት ኪሎ ፕላዛ አካባቢ በተሰራው የመናፈሻ ቦታ ላይ ፎቶ ሲነሳ ያገኘነው ወጣት ነው። ከተማዋ ለኑሮ ተስማሚ እና ለመዝናኛ ተመራጭ እየሆነች መምጣቷን ጠቁሞ፣ በሚንቀሳቀስባቸው ቦታዎች፣ መናፈሻዎች እና ፋውንቴኖች ላይ ቆሞ ፎቶ እንደሚነሳ ይናገራል።
በከተማዋ የተሰሩት የብስክሌት፣ የእግረኛ መንገዶች እንዲሁም የመናፈሻ ቦታዎች ሳቢና ማራኪ ሆነው በመሰራታቸው ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት ከመፍጠራቸው በተጨማሪ ነዋሪዎቹ በመዝናናት መንፈሳቸውን ያድሳሉ። ነዋሪዎቹ ቅዳሜና እሁድ የእረፍት ጊዜያቸውን የሚያሳልፍባቸው ቦታዎች በየቦታው ተሰርተዋል፡፡ ይህም በፎቶ ግራፍ የሚገኘውን ገቢ አሳድጎታል ብሏል፡፡
ወጣት ሀብታሙ በፊት የነበረው መንገድ እንኳን ቆሞ ፎቶ ግራፍ ለመነሳት ይቅርና ለመሄድም የማይመች ነበር ብሎ፣ አሁን ግን በመናፈሻ ቦታዎች በመግባት ለቦታ ሳይከፍል ፎቶ መነሳቱ ደስታን ፈጥሮልኛል ሲል አክሏል፡፡
ፎቶ ግራፍ ለረጅም ጊዜ አብሮ የሚቆይ በመሆኑ የከተማዋን እድገት ምን እንደምትመስል፣ የት እንደደረሰች ለትውልድ ለማሳየት ይጠቅማል ባይ ነው። የኮሪደር ልማት በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል፣ አንድን ከተማ ዓለም አቀፍ የከተማ ደረጃን ጠብቆ ማልማት እንደሚቻል የታየበት ነው። ህብረተሰቡ ልማቱ እንዲሳካ የነቃ ተሳትፎ ያደረገ ሲሆን ከውጤቱም ተጠቃሚ እየሆነ መጥቷል። የኮሪደር ልማቱ ማህበራዊ ልማትን በማፋጠንና ዘመናዊ የንግድ ማዕከላትን በመገንባት ኢኮኖሚውን እያነቃቃ ነው። በዚህም ንግድንና ኢንቨስትመንትን ይበልጥ ሳቢ በማድረግ ለነዋሪዎቹ የስራ ዕድል እየፈጠረ ይገኛል፡፡
በይግለጡ ጓዴ