ለምክር ቤቶቹ የቀረበው የፕሬዝደንቱ ንግግርአንኳር ጉዳዮች

You are currently viewing ለምክር ቤቶቹ የቀረበው የፕሬዝደንቱ ንግግርአንኳር ጉዳዮች

ባሳለፍነው ሰኞ  መስከረም 26 ቀን 2018 ዓ.ም. 6ኛው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ስነሥርዓት መከናወኑ ይታወሳል፡፡ በስነሥርዓቱ ላይ የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ለሁለቱ ምክር ቤቶች  የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡ በንግግራቸውም ከለውጡ በኋላ፤ በተለይም በ2016 እና 2017 በጀት ዓመት እንደሀገር የተመዘገቡ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ የሠላምና ደህንነት ስኬቶችን እና ፈተናዎችን አንስተዋል፡፡ በ2018 በጀት ዓመት የታቀዱ ቁልፍ ጉዳዮችንም አመላክተዋል፡፡

ፕሬዝዳንቱ ንግግራቸውን የጀመሩት ይህ ዘመን በታሪካችን ውስጥ በጉልህ የሚወሳ አዲስ ምዕራፍ ተደርጎ የሚወሰድ መሆኑን በማንሳት ነው፡፡ ለዚህም ካነሷቸው ምክንያቶች መካከል፡- በአዲሱ ዓመት መባቻ የበርካታ ዓመታት ቁጭታችንን መቋጫ እና የጥረታችን ውጤት የሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቁ፣ በወርሃ መስከረም መጀመሪያ ላይ ደግሞ የኢትዮጵያ የከርሰ ምድር ሃብት የብስራት ጅማሮ የሆነው የተፈጥሮ ጋዝ የወጣበት እንዲሁም ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ የተጀመረበት ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ 

“መንግስት ለዓመታት ሲያጠናና ሲዘጋጅበት ቆይቶ ተግባራዊ ባደረገው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እንዲሁም ቀደም ሲል በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ማዕቀፍ ተያይዘው በተከታታይ ዓመታት ተግባራዊ ሲደረጉ በቆዩ ፕሮግራሞች ኢኮኖሚያችን በማንሰራራት ላይ ይገኛል” ያሉት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት፤ ከለውጡ በፊት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለዘመናት በመዋቅራዊ ተግዳሮቶች ተፅዕኖ ውስጥ ወድቆ በከፍተኛ የዕዳ ጫና ውስጥ የሚገኝ፣ የነበረው ዕድገትም በዘላቂ የፋይናንስ መሰረት ላይ ያልተዋቀረ እንዲሁም የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶችን የፈጠረ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

የኢፌዴሪ ፕሬዚደንት ታዬ በንግግራቸው እንዳነሱት፤ በ2010 ዓ.ም. ወደ ስልጣን የመጣው የለውጡ መንግስት ቀደም ሲል የነበሩ ሀገራዊ የኢኮኖሚ መዛባቶች የሚያርሙና ወደ ብልፅግና ጎዳና የሚያደርሱ ፈጣንና መጠነሰፊ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ተግባራዊ አድርጓል፡፡ የወጪ ንግድ(ኤክስፖርት) እንዲሁም የውጭ ምንዛሬ ክምችት አድጓል፡፡ የልማት አቅጣጫዎች ትኩረት ውሱን ከሆኑ ዘርፎች ወደ ባለብዙ ዘርፍ የኢኮኖሚ መሰረቶች እየተቀየረ ይገኛል፡፡ ኢኮኖሚውን ከዕዳ ጥገኝነት በማላቀቅ ወደ ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት ለማሸጋገር የሚያስችል ወሳኝ ምዕራፍ ተከፍቷል፡፡ ያሉንን አቅሞች ማወቅ፣ በችግር ውስጥ መልካም ዕድልን ማየት፣ በፈጠራና በፍጥነት፣ በትብብርና የተለያዩ አቅሞችን በማሰባሰብ እንዲሁም ዘላቂ ግቦችን ማሳካት የኢኮኖሚ ለውጡ መሰረት ትኩረቶች ናቸው፡፡ ይህም በመሆኑ አጠቃላይ ሀገራዊ እድገት ተፋጥኗል፡፡

ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በ2017 በጀት ዓመት 9 ነጥብ 2 በመቶ ጥቅል ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገቧን ያነሱት ፕሬዝዳንቱ ለዕድገቱ አስተዋፅኦ ያደረጉ ዘርፎችን ዘርዝረዋል፡፡ እንደሳቸው ማብራሪያ፤ በግብርናው ዘርፍ በ2017 ምርት ዘመን 1 ነጥብ 57 ቢሊዮን ኩንታል ምርት ተመርቷል፡፡ ይህም ከቀደመው ዓመት (በ2016 የምርት ዘመን ተመርቶ ከነበረው የ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ኩንታል ምርት) ጋር ሲነፃፀር የ24 ነጥብ 7 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም ከ59 በመቶ ወደ 65 በመቶ አድጓል፡፡ የወርቅ ምርት በ2016 በጀት ዓመት ከነበረበት 3 ነጥብ 9 ቶን፤ በ2017 በጀት ዓመት ወደ 38 ነጥብ 87 ቶን ማሳደግ ተችሏል፡፡ የሲሚንቶ ምርት በ2016 በጀት ዓመት 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቶን የነበረ ሲሆን፤ በ2017 በጀት ዓመት ወደ 9 ነጥብ 1 ሚሊዮን ቶን ከፍ ብሏል። ከ150 በላይ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች በሀገራችን ተካሂደዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፤ የዲጂታል ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ፣ የውጭ ንግድ ተሳትፎ፣ የኑሮ ውድነትን የመቀነስ ሥራ አበረታች መሻሻሎች የታዩባቸው ስለመሆናቸው በምክር ቤቶቹ የጋራ ስብሰባ የመክፈቻ ስነሥርዓት ላይ ተነስቷል፡፡ በፕሬዝዳንቱ እንደተብራራው፤ በ2017 በጀት ዓመት የባንክ ብድር 822 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ተለቋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ሦስት አራተኛው ወይም 77 በመቶው ለግሉ ዘርፍ የተሰጠ ብድር ነው፡፡

ከውጭ ንግድ(ኤክስፖርት) በ2017 በጀት ዓመት 8 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡ ይህም ከ2016 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ116 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡  የኑሮ ውድነትን ለመቀነስ በተደረገው ተከታታይ ጥረት ዋጋ ንረት በ2016 በጀት ዓመት የሰኔ ወር 19 ነጥብ 9 በመቶ የነበረ ሲሆን፤ በ2017 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወር ላይ 13 ነጥብ 9 በመቶ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ለመንግስት ሠራተኞች የደመወዝ ማሻሻያ በማድረግ 4 ሺህ 760 የነበረውን ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ወደ 6 ሺህ ብር ማሳደግ ተችሏል፡፡ በ2017 በጀት ዓመት መንግስት ከብሔራዊ ባንክ ምንም ዓይነት የቀጥታ ብድር ሳይወስድ በጀት ዓመቱን አጠናቅቋል።

ማህበራዊ ዘርፍ

መንግስት በማህበራዊው ዘርፍ ውጤት እንዲመጣ በትምህርት እና በጤና መስኮች ላይ ችግርንና ክፍተትን የለየ ሥራ መሠራቱ ተጠቁሟል። እያንዳንዱ ሀገራዊ እንቅስቃሴ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ እንዲሆን ጥረት መደረጉም ተነስቷል። በዚህም አመርቂና አበረታች ውጤት መምጣታቸው በፕሬዝዳንቱ ንግግር ተካትቶ ቀርቧል፡፡ በዚሁ መሰረት፤ በትውልድ መካከል ለሚከሰተው የእሴት መሸርሸር ዋነኛው ምክንያት የትምህርት ጥራት ችግር ነው፡፡ ይህንን ሳንካ ለመቅረፍ በ2017 የትምህርት ዘመን ለትምህርት ጥራት ትኩረት ተሰጥቷል። መንግስት የትምህርትንና ስልጠና ፖሊሲ ቀርጾ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ነው፡፡ “ትምህርት ለትውልድ” በሚል መሪ ቃል ማህበረሰቡን በማንቀሳቀስ የትምህርት ተደራሽነትን የማሳደግ ሥራ ተሠርቷል። ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ተማሪዎች በትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ከትምህርት ገበታ እንዳይቀሩ አድርጓል። ይህ ጉልህ ተግባር በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ዕውቅና ተሰጥቶታል፡፡

ባለፉት ዓመታት በጤናው ዘርፍ የተገኙትን ስኬቶች መነሻ በማድረግ ክፍተቶችን የመሙላት ሥራ አተኩሮ መሥራቱ በምክር ቤቶቹ የመክፈቻ ስነሥርዓት ላይ በቀረበው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ንግግር ተጠቅሷል፡፡ የለውጡ መንግስት፤ በሽታን ከመከላከል ባለፈ አክሞ በማዳን ላይ ልዩ ትኩረት ማድረጉ ተነስቷል፡፡ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር የህክምና መሣሪያዎችንና መድሃኒቶችን በሀገር ውስጥ ማምረት በመቻሉ ከፍተኛ ውጤት መገኘቱ ተገልጿል፡፡

ህፃናት፣ ሴቶች፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች አረጋዊያን እንዲሁም የሀገር ባለውለታዎችን ታሳቢ ያደረጉ ተግባራትን በብዛት እና በጥራት በማከናወን መንግስት አካታችነት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራቱን በተግባር ስለማረጋገጡ በኢፊዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ ንግግር ተካትቶ ቀርቧል፡፡ በዚህ ንግግር ውስጥ እንደተብራራው፤ ባለፉት ዓመታት መንግስት በሠራው ሥራ ሴቶችና ወጣቶችን ወደ አመራርነት በማምጣት ውሳኔ ሰጭነታቸው እንዲጨምር ተደርጓል፡፡ ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች በነገዋ የማገገሚያ እና የክህሎት ማዕከል በማሰልጠን ተሳትፏቸው እንዲጨምር ተደርጓል። የወጣቶችን ክህሎት በማጎልበት የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር የሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። የወጣቶችን አዕምሯዊና አካላዊ ዕድገት ማሻሻል የሚያስችሉ የስፖርት ማዘውተሪያዎች ተገንብተዋል፤ ለአገልግሎትም በቅተዋል፡፡ ለአካል ጉዳተኞች ከተሰጡት በርካታ ድጋፎች መካከል የዓይነስውራን ትምህርት ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት እንዲሰጡ መደረጋቸው በአብነት ይጠቀሳል፡፡ በሕጻናት እድገትና ትምህርት ላይ በተለየ ሁኔታ እየተሠራ ያለው ሥራ መንግስት ለመጪው ትውልድ ሰፊ ትኩረት መስጠቱን የሚያመላክት ነው፡፡

የውጭ ግንኙነት

“ብሔራዊ ጥቅም እና የዜጎች ክብር” የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ዋነኛ ማዕከልና መሰረታዊ ማጠንጠኛ ተደርጎ በመሠራቱ፤ ባለፉት ዓመታት የአገሪቷ ጂኦስትራቴጂያዊ ቁመና በመደርጀት ላይ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ በንግግራቸው አካትተው ለሁለቱ ምክር ቤቶች አቅርበዋል፡፡ አያይዘው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ እየተከተለችው ባለው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ምክንያት ከታዛቢነት ወደ አጀንዳ ተላሚነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት መሸጋገር ችላለች፡፡

“አገራችን በድንበር ተሻጋሪ ሃብቶቿ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ስትቀበል፤ በዚያው ልኬትም አስተማማኝ የባሕር በር የማግኘት መብቷን ማረጋገጥ ይኖርባታል። የኢትዮጵያ ሕልውና መሰረት በሆኑት በሁለቱም ታላላቅ የውሃ ሃብቶች ዙሪያ መንግስት ያልተቋረጠ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል” ያሉት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት  እስካሁን በተደረጉ ጥረቶች ሦስት ጉልህ ውጤቶች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል። እነዚህም ውጤቶች አንደኛው፤ የታላቁ ኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አጋጥመውት የነበሩትን ፈተናዎች በጥበብ በማለፍ ማጠናቀቅና በደመቀ ስነሥርዓት ማስመረቅ መቻሉ ነው፡፡ ሁለተኛው፤ አስተማማኝ እና ዘላቂነት ያለው የባሕር በር የማግኘት ጉዳይ ከፍ ወዳለ ደረጃ መሸጋገሩ ነው፡፡ ይህም የሀገራችን ፍትሃዊ ጥያቄ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ እያደገ የመጣ ቅቡልነት አስገኝቷል፡፡ ሦስተኛው፤ በውጭ ሀገር ለሚኖሩ እና ለችግር የተጋለጡ ዜጎች በክብር ወደ ሀገራቸው መመለስ መቻሉ ነው፡፡ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሀገራቸው ልማት ላይ ይሳተፉ ዘንድ ጥረቶች ተደርገዋል፡፡

የ2018 በጀት ዓመት የመንግስት ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች

በኢትዮጵያ የተጀመረውን የማንሰራራት ጉዞ በጽኑ መሰረት ላይ እንዲገነባ በ2018 በጀት ዓመት በመንግስት ሊሠሩ ይገባቸዋል ተብለው የተለዩ ቁልፍ ጉዳዮችን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀስላሴ በዝርዝር አብራርተዋል፡፡ ተቋማዊ ግንባታ፣ ሀገራዊ ሠላምና ጸጥታ፣ አገልግሎት አሰጣጥና መልካም አስተዳደር፣ የፍትሕ ሥርዓቱን ለማሻሻል እንደሚሠራም ጠቁመዋል። ይህንንም አስመልክቶ በንግግራቸው እንዳብራሩት፤ ከሥርዓት መለዋወጥ ጋር የማይናዱ ነፃ፣ ገለልተኛና ሕዝባዊ ብሔራዊ ተቋማት ለመፍጠር መንግስት ፅኑ መሰረት ላይ ይገኛል፡፡ በያዝነው በጀት ዓመትም አንድነትንና ሰላምን በማይናወጥ መሰረት ላይ ለማድረስ መንግስት በተቋማት ግንባታ ላይ አበክሮ ይሠራል፡፡ ብሔራዊ የፀጥታና የደህንነት ተቋሞቻችን የሥርዓት ለውጥን የሚሻገሩ እና የሀገርን ቀጣይነት የሚያረጋግጡ ብርቱ ተቋማት እንዲሆኑ መንግስት በቁርጠኝነት ይተጋል፡፡

“በየቦታው የሚታዩ ግጭቶችን በኃይል ማረቅ፣ ማስተካከል የሚቻል ቢሆንም፤ ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው ግን በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሆነ መንግስት በፅኑ ያምናል” ያሉት የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንቱ፤ የዕርቅ እና የምክክር ሰላማዊ አማራጮችን በመጠቀም የሀገሪቷን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ እየሠራ እንደሚገኝ አስረድተዋል። በየጊዜው የሚስተዋሉ የኃይል እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም መንግስት ሙሉ ዝግጁነት እና ዘመናዊ አቅም ቢኖረውም “የዛሬውን ግጭት በማሸነፍ ለነገው ትውልድ ቂምና ቁርሾ አናወርስም” የሚል መርህን በመከተል በዛሬ ብልሃትና ትዕግስት ለነገ ዘላቂ ሰላም የሚበጅ አካሄድን መምረጡንም አንስተዋል፡፡ ይህ የመንግስት አካሄድ ሀገራዊ ሰላምን ለመትከል፣ ዘላቂና ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስትን ለመመስረት ያለው ፋይዳ ትልቅ ነውም ብለዋል፡፡

ለአገራዊ ምክክሩ መሳካት መላው ሕዝባችን እንዲሁም ሊሂቃን የበኩላቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት አክለው እንደገለፁት፤ “ለሕዝብ የቀረበ እና ለሕግ የታመነ አስተዳደር ወደ ብልፅግና ለሚደረገው ጉዞ ወሳኝ ነው። ይህንንም እውን ለማድረግ መንግስት የአስተዳደር ማዕቀፎችን በማሻሻል፣ የተቋማትን ቅንጅት በማጠናከር እንዲሁም ተመሳሳይነት ተጓዳኝ ዘርፎችን በማሰባሰብ ውጤታማ እንዲሆኑ አድርጓል፡፡ የሕዝብ አገልግሎት ለማዘመን በ2025ቱ የዲጂታል ኢትዮጵያ ትልም መሰረት አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል። በቀጣይም በ2030 ዲጂታል ስትራቴጂ፤ ይህንን ውጤት ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ ይሠራል፡፡ ሁሉንም አገልግሎቶች ዲጂታል በሆነ አግባብ ለመስጠት የተጀመረው የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተጠናክሮና ተስፋፍቶ ይቀጥላል፡፡ የመረጃ አሰባሰብ እና አተናተን ሥራ በላቁ ቴክኖሎጂዎች በማዘመን በመረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ አፈፃፀም በማጎልበት የመረጃ ሉዓላዊ አቅም ይገነባል”፡፡

መንግስት የዜጎችን ዋስትና የሚያስጠብቅ የፍትሕ ስርዓት ለመዘርጋት በ2018 በጀት ዓመት በትጋት ይሠራል፡፡ የተሻሻሉት የወንጀል እና የፍትሐብሔር ህጎች በቴኖሎጂ እንዲዘምኑ ተደርጓል፡፡ የፍርድ ቤቶችን አሠራር ለማሻሻል የተጀመሩ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ትግበራዎችን በማስፋት፣ በማሟላት እና በማሳደግ ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡ ባሕላዊ የፍትህ አማራጮች በአሠራር ጎልብተው በፍትሕ ስርዓት ውስጥ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ የተጀመረው አሠራር ይቀጥላል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በመንግስት በ2018 በጀት ዓመት ሊሠሩ የታቀዱ ተግባራትን አንደሚከተለው ዘርዝረዋል። ፕሬዝዳንቱ እንደተናገሩት በ2018 በጀት ዓመት 9 በመቶ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት እድገት ለማረጋገጥ ታቅዷል፡፡ መንግስት ምርትን በመጠንም በጥራትም ያሳድጋል፡፡ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ፣ ቁጠባና ኢንቨስትመንትን ያበረታታል፡፡ ግብርናን ከተፈጥሮ ጥገኛነት ለማውጣት ይሠራል፡፡ ለተፈጥሮ ጥገኛነት እና ለውጪ ጫና  የማይንበረከክ ኢኮኖሚን ይገነባል፡፡ የዋጋ ግሽበት ወደ ነጠላ አሃዝ ለማውረድ ይሠራል፡፡ ከፍተኛ የሥራ ዕድልን በሀገር ውስጥ እና በውጭ አማራጮች መፍጠር፡፡ ግብርናው የ6 ነጥብ 8 በመቶ እድገት እንዲያስመዘግብ ይሠራል። የምግብ ዋስትናንና የምግብ ሉዓላዊነትን ያፀናል። የከተሞች ልማትን በኮሪደር ልማት እና በተቀናጀ የመሰረተ ልማት ግንባታን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

 በመንግስት እና በግሉ ዘርፍ የጋራ ትብብር የከተሞች የቤት አቅርቦት ይቀረፋል፡፡ በገጠርም የመኖሪያ ቤቶች ደረጃ እንዲሻሻል ይደረጋል። የቱሪዝም መዳረሻዎችን በማልማት፣ በማስፋፋት እና መሰረተ ልማቶችን በማሟላት ከቱሪዝም ዘርፍ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ ይሠራል፡፡ የማዕድን ዘርፍ አንዱ ኢኮኖሚ ምሰሶ ሆኖ ይቀጥል ዘንድ፤ የከርሰ ምድር ሃብት ለሕዝብ ጥቅም እንዲውሉ ይሠራል። እሴት የተጨመሩ ምርቶች ለገበያ እንዲቀርቡ ይደረጋል፡፡ የተመጣጠነ የመሰረተ ልማት ስርጭትን ለማረጋገጥ ይሠራል።  በሁሉም የሀገራችን ክፍሎች የኤሌክትሪክ እና የቴሌኮሙኒኬሽን ተደራሽነት እንዲረጋገጥ ይሠራል። የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ጥራታቸውን የጠበቁ የቅድመ መደበኛ እና የመደበኛ ትምህርት ተቋማትን ይገነባል። የጤና ተቋማትን ተደራሽነትና ጥራት ለማሳደግ ይሠራል፡፡ ሁሉም እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ እና ህፃናት ሁሉንም ክትባቶች እንዲከተቡ ይደረጋል፡፡ ወደከተማ የሚደረጉ ፍልሰቶች እንዲቀንሱ ይሠራል፡፡

በተጨማሪም፤ ኢትዮጵያ በዐባይ እና በቀይ ባህር ማዕከል የምትገኝ ሀገር ነች፡፡ ህልውናዋም በሁለቱ ውሃዎች ተጠቃሚነቷ ይወሰናል፡፡ ስለዚህ የባሕር በር እና የዐባይ  ጉዳይ በዲፕሎማሲያዊና ሰላማዊ አማካኝነት ይሠራል፡፡ በውጭ ግንኙነት ፖሊሲው ቅድሚያ ለጎረቤት ሀገር የሚለውን መርህ አጠናክሮ ይቀጥላል። በዓለም አቀፍ የኃይል አሰላለፎችን ሚዛኑን በመጠበቅ ትብብርና ሠላምን ያስቀደሙ ግንኙነቶችን ለማስፋት ይተጋል። የኢትዮጵያ ተደማጭነትና ተፅዕኖ በዓለም መድረክ እንዲያድግ ይሠራል። ሀራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ነፃ፣ ገለልተኛ፣ ፍትሃዊ፣ ተዓማኒና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ይሠራል፡፡

በደረጀ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review